በኢትዮጵያ ሙያዊነትን የጠበቀ የፖሊስ አገልግሎት ለማጎልበት የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወሳኝ ሚና አላቸው-ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ሙያዊነትን የጠበቀ የፖሊስ አገልግሎት ለማጎልበት የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወሳኝ ሚና አላቸው-ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሙያዊነትን የጠበቀ የፖሊስ አገልግሎት ለማጎልበት የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ 5ኛውን ሀገር አቀፍ የጥናት ሲምፖዚየም ዛሬ ሰንዳፋ በሚገኘው የዩኒቨርሲቲው ዋና መስሪያ ቤት ማካሄድ ጀምሯል።
በሲፖዚየሙ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አመራር አባላት፣ የክልል ፖሊስ ተቋማትና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ተገኝተዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው የጥናት ሲምፖዚየም በዩኒቨርሲቲውና በሌሎች ትምህርት ተቋማት ባለሙያዎች የተሰሩ 17 ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።
ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የፖሊስ አገልግሎትን ለማዘመን መሰረታዊ ለውጦች እየተካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምና ፀጥታ ማስፈን የሚያስችሉ የወንጀል መከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ በጥናት ላይ የተመሰረቱ መፍትሔዎችም እየተተገበሩ መሆኑን አንስተዋል።
የጥናትና ምርምር ስራዎች የፖሊስ የለውጥ ስራዎችን ውጤታማ የሚያደርጉና ተቋማዊ የወንጀል መከላከል አቅም የሚያጎለብቱ መሆን እንዳለባቸውም ነው ኮሚሽነር ጄነራሉ ያነሱት።
የፖሊስ ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱን ፖሊስ የዘመነ አገልገሎት እንዲሰጥ በማድረግ በኩል ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ስራዎችን በማከናወንና ጥናቶችን ወደ ተግባር በመለወጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የፖሊስ አገልግሎት ጠንካራ፣ በእውቀትና በሙያዊነት እንዲመራ ለማድረግ እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ የስልጠና ተቋማትን ሙያዊ ደረጃቸውን ወጥ የማድረግና የማሻሻል ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
በዚህም በክልሎች የሚገኙ የፖሊስ አካዳሚዎች ከመደበኛው ስልጠና ጀምሮ ተመሳሳይና ሀገራዊና ወጥ የትምህርት ስርዓት እንዲተገብሩ ይደረጋል ነው ያሉት።
የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀትን የሚያስቀር ለውጥ እንደተደረገው ሁሉ ለተሻለ ሀገራዊ አንድነት የሚበጅ ወጥ የፖሊስ ትምህርትና ስልጠና ሂደት በቀጣይ ዓመት እንደሚጀመርም ኮሚሽነር ጄነራሩ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መስፍን አበበ በበኩላቸው፤ ጥናቶች የሀገር ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን ተግዳሮቶችንና የመፍትሔ ሀሳቦችን በመጠቆም እንደሚያግዙ ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲው እንደ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲነቱ በቀጣይ በሰላምና ፀጥታ ላይ ሳይንሳዊና ችግር ፈቺ ጥናቶችን በትኩረት እንደሚያካሂድ አረጋግጠዋል።