ኦሜድላ በወንዶች አዲስ አበባ ፖሊስ በሴቶች የዘንድሮው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና አጠቃላይ አሸናፊ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
ኦሜድላ በወንዶች አዲስ አበባ ፖሊስ በሴቶች የዘንድሮው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና አጠቃላይ አሸናፊ ሆኑ
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2015(ኢዜአ)፦ ኦሜድላ በወንዶች አዲስ አበባ ፖሊስ በሴቶች የዘንድሮው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና አጠቃላይ አሸናፊ ሆነዋል።
ከሰኔ 15 አንስቶ በራስ ኃይሉ ስፖርት ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የዘንድሮው ሶስተኛ እና የመጨረሻ ዙር የብሔራዊ የቦክስ ሻምፒዮና ትናንት ፍጻሜውን አግኝቷል።
በሻምፒዮናው ኦሜድላ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ እና የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተሳትፈዋል።
በወንዶች ከ48 እስከ 92 ኪሎ ግራም በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 52 ኪሎ ግራም ሻምፒዮናው የተካሄደባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።
በሶስተኛው ዙር ሻምፒዮና በወንዶች ኦሜድላ በሴቶች የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አሸንፈዋል።
በቦክስ ውድድሮቹ የተገኘው አጠቃላይ ውጤት ተሰልቶ በሁለቱም ጾታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ክለቦችም ተለይተዋል።
በዚሁ መሰረት በወንዶች ኦሜድላ በሴቶች አዲስ አበባ ፖሊስ የዘንድሮው ዓመት ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ እና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የዘንድሮው የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮና የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዙር ውድደር በአዲስ አበባ እና ወላይታ ሶዶ ከተሞች መካሄዱ ይታወቃል።