የስፖርት ቤተሰቦች በህዝቦች መካከል አንድነትና ፍቅርን በማጠናከር የሀገርን መልካም ገጽታ ለማስታዋወቅ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ቤተሰቦች በህዝቦች መካከል አንድነትና ፍቅርን በማጠናከር የሀገርን መልካም ገጽታ ለማስታዋወቅ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል
መቀሌ ሰኔ 18/2015 (ኢዜአ) በህዝቦች መካከል አንድነትና ፍቅርን በማጠናከር የሀገርን መልካም ገጽታ ለማስታዋወቅ የስፖርት ቤተሰቦች ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሸን ፕሬዝዳንት አቶ ወንድሙ ሃይሌ አስታወቁ።
በመቀሌ ከተማ ሲካሄድ የቆየውና ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተሳተፉበት የ2015 የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር ዛሬ ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሸን ፕሬዝዳንት አቶ ወንድሙ ሃይሌ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት ፍቅርና አንድነትን ለማረጋገጥ፣ ጤናና ልማትን ለማምጣትና የአገር መልካም ገፅታን ለማስተዋወቅ ስፖርት ትልቅ ሚና አለው።
“በዚህም በህዝቦች መካከል አንድነትና ፍቅርን በማጠናከር የሀገርን መልካም ገጽታ ለማስታዋወቅ የስፖርት ቤተሰቦች ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል” ብለዋል።
ለስፖርት ዘርፉ ልዩ ትክረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ኮኮብ ብስክሌተኞች ተብለው የተመረጡ ስፖርተኞችም በቀጣይ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ውድድር ውጤታማ ሆነው ለመመለስ ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።
በመቀሌ የተካየሄደው የ2015 የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር በደመቀ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ፕሬዝዳንቱ አመሰግነዋል።
ዛሬ በተካሄደው የማጠናቀቂያ ስነ ስርዓት በወንዶች 120 ኪሎሜትርና በሴቶች 60 ኪሎሜትር የከተማ ብስክሌት ውድድር ተካሄዷል።
በወንዶች በተካሄደ የ120 ኪሎሜትር ውድድር የትግራይ ክልልን ወክለው የተሳተፉ፥ ቡዛየ ተስፉ፣ ፅጋቡ ገብረማርያምና ሙሉ ክንፈ በቅደም ተከተላቸው መሰረት ከአንደኛ እሰከ ሶስተኛ ደረጃ ተከታትለው በመግባት የወርቅ፣ብርና የነሃስ ሜዳሊያ ተሸልመዋል።
በተመሳሳይ በሴቶች በተካሄደው 60 ኪሎሜትር የከተማ ውድድርም ከትግራይ ክልል ትርሃስ ተክላይ፣ ሰላም አመሃና አዜብ ካህሳይ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት የወርቅ፣ የብርና የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።
ከሰኔ 14 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በመቀሌ በተካሄደው የ2015 የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር የመቀሌ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎችና የስፖርት ቤተሰቦች ተከታትለዋል።