"ዓባይ ፪" መርከብ አቀባበል ተደረገላት - ኢዜአ አማርኛ
"ዓባይ ፪" መርከብ አቀባበል ተደረገላት
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2015 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ታሪክ ግዙፏ "ዓባይ ፪" መርከብ አቀባበል እንደተደረገላት ተገለጸ።
በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ታሪክ ግዙፏ "ዓባይ ፪" መርከብ በዛሬው ዕለት በጅቡቲ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላታል።
በስነ ስርዓቱ ላይ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ የጅቡቲ ሪፐብሊክ የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ሀሰን ኢብራሂም፣ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት የሺፒንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ካፒቴን ወንድወሰን ካሳ እና የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
"ዓባይ ፪" መርከብ በቻይናው ያንግዡ ዳያንግ ሺፕ ቢዩልዲንግ የተገነባች ሲሆን፤ 200 ሜትር ርዝመት እና 63 ሺህ 229 ቶን የመጫን አቅም እንዳላት ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ታሪክ በግዙፍነቷ አቻ የለሽ የሆነቸው ይህች መርከብ የባሕር ትራንስፖርት ስራን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደምታሸጋግርም ተመላክቷል።
"ዓባይ ፪" መርከብ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ድርጅትን ለኪሳራ ዳርገው በነበሩት 42 ሺህ ቶን የመጫን አቅም ባላቸው ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የተቀየረች መሆኗን የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል።