ማረሚያ ቤቶች የህግ ታራሚዎችን መረጃ አያያዝ ስርዓት ማዘመን ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ማረሚያ ቤቶች የህግ ታራሚዎችን መረጃ አያያዝ ስርዓት ማዘመን ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2015 (ኢዜአ) ፦ ማረሚያ ቤቶች የህግ ታራሚዎችንና በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎችን መረጃ አያያዝ ስርዓት ማዘመን ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስገነዘበ።
ለህግ ታራሚዎች የሚሰጠው የቀለም ትምህርትና የክህሎት ስልጠና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው ኮሚሽኑ ጥሪ ያቀረበው፡፡
ኮሚሽኑ በህግ ታራሚዎች እና በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ በማረሚያ ቤቶች ባካሄደው የክትትል ስራ የተገኙ ግኝቶችና ምክረ ሀሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
በመድረኩ ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በተመረጡ 37 ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች ሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ያደረገውን የክትትል ግኝቶች ይፋ አድርጓል።
መረጃው በአካል ምልከታ፣ የተለያዩ ሰነዶችን በመመልከት፣ ከታራሚዎች እና ከማረሚያ ቤቶች አመራሮች ጋር በተደረጉ ቃለመጠይቆች እና ውይይቶች መደራጀቱ ተገልጿል።
በዚህም የታራሚዎች መረጃ አያያዝ በዲጅታል ስርዓት አለመዘመን ኮሚሽኑ በክፍተት ከለያቸው ችግሮች መካከል ተጠቅሷል።
በተጨማሪም የማረሚያ ቤቱን ዓላማ፣ መተዳደሪያ ህግ እና ደንብ በማሳወቅ ረገድ ክትትል በተደረገባቸው ሁሉም ማረሚያ ቤቶች ውስንነት ሰለመኖሩም ተመልክቷል።
እንዲሁም ታራሚዎችን በፈርጅ ከመለየት አንፃር በተለይ በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች በፍርድ መጠን፣ በእድሜ፣ በጤና ሁኔታ፣ በወንጀል ታሪክ እና ህግ ጥበቃ ስር የዋሉበት ምክንያትን መሰረት አድርጎ መረጃ ያለመያዝ ክፍተቶች መኖራቸውንም አመላክቷል።
በሌላ በኩል በክትትሉ ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን በፍርድ ቤት ትእዛዝ መቀበልና ለአካል ብቃት እንቅስቃሴና መዝናኛ የሰጡት ትኩረት በሪፖርቱ በጥንካሬ ከተወሰዱ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
በታራሚዎች እና ማረሚያ ቤቶች መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻል ማሳየቱንም ከሚሽኑ ጠቁሟል፡፡
በሁሉም ማረሚያ ቤቶች ለቀለም ትምህርት ትኩረት መሰጠቱ በጥንካሬ ከተነሱት መካከል ይገኙበታል።
ግኝቱ በሰጠው ምክረ ሀሳብ መሰረትም ማረሚያ ቤቶች የህግ ታራሚዎችንና በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎችን መረጃ አያያዝ ስርዓት ማዘመን እንደሚገባቸው ጠቁሟል።
በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች ከውሀ አቅርቦት እጥረት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ በሪፖረቱ ምክረ ሀሳብ ላይ ቀርቧል።
በተጨማሪም ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን ባገናዘበ መልኩ የቀለም እና የሙያ ስልጠና መስጠት እንደሚገባቸውም አመላክቷል።
እንዲሁም የታራሚዎችን አያያዝ ለማሻሻል ይረዳ ዘንድ በቂ በጀት፣ ቁሳቁስ እና የሰው ሀይል እንዲኖራቸው የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ጠቁሟል።
የኦሮሚያ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብራሂም ሀጂ በበኩላቸው፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ታራሚዎች በማረሚያ ቤቶች ቆይታቸውን ያለምንም ሰብአዊ መብት ጥሰት አጠናቀው እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ከጤና እና ከትምህርት አንጻር ክፍቶችን ለመሙላት ስራዎች እየተሰሩ ሰለመሆኑ ተናግረዋል።
ከመረጃ አያያዝ ስርአት ጋር በተያያዘም መረጃዎችን ወደ አንድ የመረጃ ቋት የማምጣትና የማዘመን ስራዎች በቀጣይ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በየጊዜው የሚያመጣቸውን ግኝቶች እና ምክረሀሳቦች መነሻ በማድረግ የማስተካከያ ስራዎች እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።