ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የተደራጀ  የፖሊስ ሀይልን በማጎልበት የህዝብን ደህንነትና የህግ የበላይነት  የማስከበሩ ተግባር ይጠናከራል- ፖሊስ ኮሚሽን

ደብረ ማርቆስ ሰኔ 18/2015(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል  የተደራጀ የፖሊስ ሀይልን በማጎልበት የህገ የበላይነትን፣  የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማስከበሩ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ በመልሶ ማደራጀት ወደ አድማ መከላከል ፖሊስ  የተቀላቀሉ የቀድሞ የልዩ ሃይል አባላትና አመራሮችን አሰልጥኖ ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ፤ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከዚህ ቀደም የልዩ ሃይል አባላት የነበሩትን በመረጡት የፌደራልና የክልሉ የጸጥታ ዘርፎች የመቀላቀል ስራ እየተካሄደ ነው።

ክልሉም ከዚህ ቀደም ወደ መደበኛና ማረሚያ ቤት ፖሊስ  የተቀላቀሉ  የቀድሞ የልዩ ሃይል አባላትን በማሰልጠን ወደ ስራ ማሰማራት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ኮሚሽነር ደጀኔ እንዳመለከቱት ፤ ወደ አድማ መከላከል ፖሊስ  የተቀላቀሉ በደብረ ማርቆስ በሚገኘው የፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ   በማሰልጠን ዛሬ ለማመስረቅ መብቃቱ አደረጃጀቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ለመሆኑ ማሳያ ነው ።

"የፖሊስ ዋነኛ ተግባር የህግ የበላይነትን ማስከበር፣ የህዝብን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ መሆኑን በቆይታችሁ ይበልጥ ግንዛቤ አግኝታችኋል፤ የናንተ መምጣት ጠንካራና የተደራጀ የፖሊስ ሃይል እንዲኖረን አስችሏል "ብለዋል።

የአድማ መከላከል ፖሊስ ከወንጀል መከላከሉ በተጓዳኝ  በተደራጀ አግባብ አድማና ግርግር የሚፈጥሩ ሃይሎች ላይ ተመጣጣኝ ሃይል በመጠቀም  መግታት መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ተወካይ ረዳት ኮሚሽነር አበበ ደለለ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ቀደም ሲል ልዩ ሃይል የነበሩት  ወደ አድማ መከላከል ፖሊስ የተቀላቀሉ አባላትን የአንድ ወር ተኩል ስልጠና በመስጠት ዛሬ ለምረቃ ማብቃታቸውን አስታውቀዋል።

በስልጠና ቆይታቸውም በህገ መንግስትና ሰብአዊ  መብት አከባበር፣ በፖሊስ ስነ-ምግባር፣ በወንጀል መከላከል፣ በምርመራ ፣ በኦፕሬሽንና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ እውቀት እንዲጨብጡ ተደርጓል ብለዋል።

ተመራቂዎቹ ክልላዊና ሀገራዊ  ወቅታዊ ሁኔታውን በመገንዘብ ማንኛውንም ፖሊሳዊ ስምሪትና ተልኮ በብቃት፣ ታማኝነትና ቁርጠኝነት ለመፈጸም መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከተመራቂዎች መካከል ረዳት ሳጅን ውዳሴ ፈንታሁን በሰጠችው አስተያየት፤ ስልጠናው ሙያዊ ፣ስነ-ልቦናዊና አካላዊ ብቃታቸውን ለማሳደግ ያስቻለ መሆኑን ተናግራለች።

ይህም ህዝባዊነትን በመላበስ ህግ በማስከበር  የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችለን በመሆኑ ደስተኛ ነኝ ብላለች።

በስልጠናው ባገኘሁት ተደማሪ እውቀትና ክህሎት እንዲሁም በነበረኝ ልምድ ህዝብንና ሀገርን ለማገልገል ቆርጨ ተነስቻለሁ ያለው ሌላው ተመራቂ ረዳት ሳጅን ይበልጣል እያሱ ነው። 

የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ላለፉት ከ30 ዓመት በላይ የፖሊስ አባላትና ከፍተኛ አመራሮችን በማሰልጠን ለክልሉ ሰላምና ደህንነት የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱን በወቅቱ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም