ቀጥታ፡

የኢትዮጵያዊያን የጋራ ምልክት ለሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን - የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራርና ሰራተኞች 

አዲስ አበባ ሰኔ 18/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያዊያን የጋራ ምልክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲሚቀጥሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ገለጸ።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን፣ ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ታላቁ የህዳሴ ግድብ የግንባታን ጎብኝተዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ፤ ጉብኝቱ  የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለፕሮጀክቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መነሳሳትን ለመፍጠር መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ የሃሳብና በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵዊያን የአንድነት ምልክት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ኢትዮጵያዊያን ከድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት ለሚያደርጉት ትግል ሁነኛ መሳሪያ ሆኖ ለሚያገለግለው ፕሮጀክት የሚያደርጉት ድጋፍ ከፍተኛ ትርጉም እንዳለው አንስተል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር፤ ኢትዮጵያዊያን በእውቀትና በገንዘብ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያስቀጥሉ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ሽያጭ፣ በ8100 እና በስጦታ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ድጋፍ መሰብሰቡን  ገልጸው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን አሻራ ያረፈበት ታላቅ አገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም  የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

የተደረገው ጉብኝትም በግንባታው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ዜጎችን በማመስገን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ድጋፍ ለማሳደግ  መነሳሳትን የፈጠረ  መሆኑን አንስተዋል።

የጉብኝቱ ተሳታፊ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮችም ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የስራ አመራር ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው ከጉብኝቱ በኋላ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር ለግድቡ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል  ይሰራል ብለዋል።

አክሽን ፎር ዘ-ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ሳሊሁ ሱልጣን በእለቱ የ300 ሺህ ብር ሶጦታ ማበርከታቸው ጠቁመዋል፡፡

አካል ጉዳተኞችን በመወከል የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የቦርድ አባል ትዕግስት አለማየሁ በጉብኝታቸው በተመለከቱት ስራ መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ ለግድቡ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ዳይሬክተር መሱድ ገበየሁ እና የ "ፕሮ ዴቬሎፕመንት ኔትወርክ" ዋና ዳይሬክተር አህመድ ሁሴን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን በትብበር ታላላቅ የልማት ስራዎችን ማከናወን አንደሚችሉ ትምህርት የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት፡፡

"ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የጎላ ተሳትፎ በማድረግ ታሪካዊ አሻራችን እናሳርፍ" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀውን ጉብኝት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶ ባለስልጣን እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መዘጋጀቱ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም