ቀጥታ፡

ባህርዳር ከተማን ወደ  ስማርት ሲቲ  ለማሸጋገር  ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ ይገባል  -  ዶክተር ድረስ ሳህሉ

ባህርዳር ፤ ሰኔ 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) ፡- ባህርዳር ከተማን ወደ ስማርት ሲቲ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት  በመደገፍ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን   ሊወጡ እንደሚገባ የከተማዋ አስተዳደር  ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ  አመለከቱ።

ከተማዋን  ስማርት ሲቲ ለማድረግ  ያለውን ምቹ ሁኔታና ተግዳሮት ላይ ያተኮረ ዓውደ ጥናት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ተካሂዷል።

በዓውደ ጥናቱ ላይ  የከተማዋ አስተዳደር  ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንደገለጹት፤ ባህርዳር ከተማን ስማርት ሲቲ ለማደረግ የተመቸች ናት።

በጣና ሃይቅና አባይ ወንዝ ዳር የተመሰረተችው  ከተማዋ ለነዋሪዎቿና ለቱሪስቶች ምቹ ከማድረግ ባሻገር ኢንቨስትመንትን በመሳብ ተመራጭ ለማድረግ የተከናወነው ስራ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ወደ ከተማዋ የሚፈልሰው የህዝብ ቁጥር  እየጨመረ በመምጣቱ ባህርዳርን  የሚመጥን ሁለንተናዊ ልማትና አገልግሎት ለማስመዝገብ የስማርት ሲቲ ግንባታን ማካሄድ አማራጭ የለውም ብለዋል።

በመልካም አስተዳደር፣ በሰላምና ደህንነት፣ በዲጅታል ቴክኖሎጅና ሌሎች የተጠኑ ዘርፎች ላይ የስማርት ሲቲ ግንባታውን በማስጀመር የሚስተዋልውን ችግር እየፈቱ በማስፋት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም   ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ  እንደሚገባ ያመለከቱት  ዶክተር ድረስ፤ የከተማ አስተዳደሩ በዋና ዋና አደባባዮች የሴኩሪቲ ካሜራ በመግጠም  ወንጀሎችን ለመከላከል  ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።  

የአማራ ክልል የከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ስሌማነ እሸቱ በበኩላቸው ፤ በክልሉ የሚገኙ ዋና ዋና ከተሞችን በሳይናንሳዊና ዘመናዊ አሰራር በመምራት ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የባህርዳር ከተማን ስማርት ሲቲ በመተግበር ለሌሎች ሞዴል ማድረግ አሁን መጀመር አለበት ብለዋል።

የከተማዋን አገልግሎት አሰጣጥ፣  የመልካም አስተዳደር አፈታት፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና ኢንቨስትመንት በስማርት ሲቲ ስርዓት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን ምዕራብ ሪጅን የገመድ አልባ ኔትወርክ ማናጀር አቶ ወርቅነህ አያልነህ፤  ባህርዳር ከተማን ስማርት ሲቲ ለማድረግ ኩባንያቸው የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል።

የከተማዋን የመልካም አስተዳደርና የልማት እንቅስቃሴ ሁሉ ወደ ዲጅታላይዜሽን ትግብራ ለመቀየር የአምስተኛ ትውልድ ኔትወርክን ለመዘርጋትና ሌሎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ አማራጮችን ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም  በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ ስድስት ክፍለ ከተሞችና ሁሉም ቀበሌዎች ወደ ዲጅታል አሰራር በመግባት ፈጣን፣ ፍትሃዊና ተገማች አገልግሎት በመስጠት በኩል ውሱንነት በመኖሩ ሊስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የባህርዳር ከተማን ስማርት ሲቲ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው በሰው ሃይል፣ በቴክኖሎጅና ሌሎች ጉዳዮች ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን  በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ሳይንትፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ቢምረው ታምራት  ገልጸዋል። 

ለዚህም ስማርት ሲቲ ሊያሟላቸው የሚገባቸው ጉዳዮችና የሚያስፈልጉ አቅርቦቶችን መለየት ተባባሪ ተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር በማዳበር በኩል የጀመረውን ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመሰለፍም ፈጥኖ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባት የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን በማጥናትና በእንደዚህ ዓይነት አውደ ጥናት በማዳበር ተግባሩን ዳር ማድረስ እንደሚገባ አመልክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም