የፀጥታ አካላት ሕዝባዊ ሚሊሻን መልሶ ለማደራጀት እና ቀደም ሲል የተጀመረው የልዩ ኃይል መልሶ የማደራጀት ሥራ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለመገምገም ያለመ ውይይት ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የፀጥታ አካላት ሕዝባዊ ሚሊሻን መልሶ ለማደራጀት እና ቀደም ሲል የተጀመረው የልዩ ኃይል መልሶ የማደራጀት ሥራ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለመገምገም ያለመ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18/2015 (ኢዜአ)፦ የፀጥታ አካላት ሕዝባዊ ሚሊሻን መልሶ ለማደራጀት እና ቀደም ሲል የተጀመረው የልዩ ኃይል መልሶ የማደራጀት ሥራ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚገመግም የውይይት መድረክ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት መካሄዱ ተገለጸ።
በውይይት መድረኩ ላይ የሀገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች እና የክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
መድረኩን የመሩት የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ናቸው።
የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ጠንካራ የፀጥታ መዋቅር ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ፤ የፀጥታ ተቋማት በተደራጀ ጥናትና ውይይት፤ በሀገራዊ ኃላፊነት ለሁላችንም የሚጠቅም አንድ ወጥ የሆነ የሠራዊት ኃይል መፍጠር ችለናል ብለዋል።
ልዩ ኃይልን መልሶ ለማደራጀት የተሰራው ሥራ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ በግምገማው መታየቱንም ተናግረዋል።
ምክትል ኢታማጆር ሹሙ አክለውም እስካሁን የተሰራው ተግባር በተቀመጠለት ዕቅድ መሠረት መከናወኑን በግምነማው ማረጋገጥ የተቻለ መሆኑን ገልፀዋል።
መልሶ የማደራጀት ሥራው እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላደረጉ ለክልል መስተዳድር፣ ለፀጥታና ለመላው ህዝብ ምስጋና አቅረበው፤ በቀጣይም የቀረውን ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።
ሕዝባዊ ሚሊሻን መልሶ በማደራጀት እና በማሰልጠን በቀበሌው ከፖሊሰ ጋር በማቀናጀት የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት እንዲጠብቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በአጽዕኖት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት በበኩላቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዋና ተግባር የሀገርን ዳር ድንበር ማስጠበቅ፣ ፖሊስ ደግሞ የሀገር ውስጥ ችግሮችን መፍታት፣ ሚሊሻው ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ የቀበሌውን የፀጥታ ተግባር ማከናወን እንዳለበት ገልጸዋል።
ሕዝባዊ ሚሊሻውን ማደራጀትና ማሰልጠን ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
አያይዘውም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስ እና ሚሊሻ ተቀናጅተው በመስራት የህዝብን ሰላምና ደህንነት ዘላቂነት በማረጋገጥ የሀገራችንን ልማት እና ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደሚገባም አስረድተዋል።