ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ 46ኛው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ዛሬ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 18/2015(ኢዜአ):- በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ፕሪሚየር ሊጉ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በኋላ ዛሬ በተስተካካይ መርሐ-ግብሮች ይመለሳል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 9 ሰአት የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ኢትዮጵያ ቡና በ38 ነጥብ 7ኛ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ59 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

በጊዜያዊው አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ እስካሁን ባደረጋቸው 27 ጨዋታዎች 9 ጊዜ ሲያሸንፍ 7 ጊዜ ተሸንፏል፤ 11 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

በ27ቱ ጨዋታዎች 35 ግቦችን ሲያስቆጥር 30 ጎሎችን አስተናግዷል።

ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ እስካሁን ባደረጋቸው 27 ጨዋታዎች በ17ቱ አሸንፎ 2 ጊዜ ተሸንፏል። 8 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመሩት ፈረሰኞቹ በሊጉ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ እርስ በእርስ ሲገናኙ የዛሬው ለ46ኛ ጊዜ ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ 21 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ኢትዮጵያ ቡና 7 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 17 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

በ45ቱ ጨዋታዎች በድምሩ 90 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ፈረሰኞቹ 61 እንዲሁም ቡናማዎቹ ደግሞ 29 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ-ግብር ባህር ዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ባህር ዳር ከተማ በ54 ነጥብ ሁለተኛ ሲሆን ሲዳማ ቡና በ35 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በዛሬ መርሐ-ግብሮች ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸንፎ ባህር ዳር ከተማ ቢሸነፍ ፈረሰኞቹ ለ16ኛ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳታቸውን ያረጋግጣሉ።

በአንጻሩ ባህር ዳር ከተማ አሸንፎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢሸነፍ በሁለቱ የዋንጫ ተፎካካሪዎች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ይላል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም