የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተደጋጋሚ የጎርፍና የድርቅ አደጋዎችን ለመከላከል ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማስፋፋት አለባቸው- የደቡብ ሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተደጋጋሚ የጎርፍና የድርቅ አደጋዎችን ለመከላከል ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማስፋፋት አለባቸው- የደቡብ ሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015 (ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ድርቅና ጎርፍን ለመከላከል የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሊያስፋፉ እንደሚገባ የደቡብ ሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴንግ ዳው ዴንግ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት ባለፉት አራት ዓመታት በተካሄደው የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 25 ቢሊዮን ችግኞችን ተክላለች።
በዚህም በጥምር ደን፣ ለምግብነት በሚውሉ የፍራፍሬ ተክሎችና ለአካባቢ ጥበቃ በሚውሉ ዛፎች አማካይነት ተጨባጭ ውጤቶች መጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሚካሄድ የሁለተኛ ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብርን በቅርቡ በአፋር ክልል አስጀምረዋል።
የደቡብ ሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴንግ ዳው ዴንግ፣ ምስራቅ አፍሪካ በተከታታይ የዝናብ እጥረት ምክንያት በድርቅ እና በአንጻሩ ደግሞ በከፍተኛ ጎርፍ የሚጠቃ አካባቢ መሆኑን በማንሳት በዚህም ሰዎች፣ እንስሳት፣ የሰብል ምርታማነት እና አጠቃላይ ስርዓተ ምህዳሩ እየተጎዳ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ባለንበት ቀጣና ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና በመቋቋም ጠንካራ ኢኮኖሚና ምቹ አካባቢን ለመፍጠር እያደረገች ያለችውን ጥረት አድንቀዋል።
በተለይም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሯ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ተከትሎ በቀጣናው የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላከል ትልቅ አቅም መሆኑን በማንሳት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትም የተቀበሉት አጀንዳ ነው ብለዋል።
ባደጉ ሀገራት በኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ በካይ ጋዞች በሚያስከትሉት የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂዎቹ እንደ ምስራቅ አፍሪካ ያሉ ታዳጊ ሀገራት መሆናቸውን አንስተዋል።
ችግሩን ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ስራን ተግባራዊ ማድረግና የአካባቢ ጥበቃ ስራ መስራት ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ፤ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ የተራቆቱ መሬቶች በደን እንዲለብሱ፣ የደረቁ ምንጮች መልሰው እንዲያገግሙ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም በምስራቅ አፍሪካ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስ የአረንጓዴ አሻራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
ደቡብ ሱዳንም በተደጋጋሚ የሚያጋጥማትን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተሞክሮን በመውሰድ የችግኝ ልማትና ተከላ እያካሄደች ነው ብለዋል።
የአካባቢው ሀገራት አንድነታቸውን በማጠናከርና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ላይ በመረባረብ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን የሚቋቋምና ከጥገኝነት የተላቀቀ ቀጣና መፍጠር እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።