ቀጥታ፡

የሠራዊቱን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ገለጹ

ሀዋሳ ሰኔ 17/2015 (ኢዜአ) የሠራዊቱን የኑሮ ሁኔታ ደረጃ በደረጃ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ መከላከያ ሚኒስቴር በ4 ቢሊዮን ብር ወጪ ለሚያስገነባው የደቡብ ግንባር ሠራዊት ሆስፒታል ዛሬ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል። 

የመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ ከ774 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባውን የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ የክፍለ ጦርና የሻለቃ መኖሪያ ካምፕና ቢሮዎችንም መርቀዋል።

በምረቃ መርሀ ግብሩ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እንዳሉት ከመከላከያ የሪፎርም ሥራዎች መካከል የሠራዊቱን ኑሮ ማሻሻል አንዱ ነው።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የመከላከያ ሠራዊት ባደረገው የሪፎርም ጥናት ስድስት ፕሮግራሞችን በመንደፍና 12 ዝርዝር ተግባራትን በማስቀመጥ ሥራ ውስጥ መግባቱን አመልክተዋል።

ከተነደፉት ፕሮግራሞቹ መካከል የሠራዊቱን ኑሮ ማሻሻል አንዱና ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ዘርፈ ብዙ መልክ እንዳለው ጠቁመዋል።

ቀደም ባለው ሥርዓት የተሰሩ የሠራዊት ካምፖች በጣት የሚቆጠሩ እንደሆኑ ያስታወሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ከለውጡ ወዲህ በርካታ የሠራዊት ካምፖችና መኖሪያ ቤቶች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

ለሠራዊቱ የተሰሩ ከፍተኛ የጤና ተቋማት ቁጥር አነስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በእዚህ በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት ለሆስፒታሎች ግንባታ ቅድሚያ ተሰጥቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

መከላከያ ሠራዊት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት አንድ ሆስፒታል ለመገንባት ከፍተኛ በጀት እንደሚጠይቅ የተናገሩት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፣ "የሠራዊቱን የምህንድስና አቅም በማጠናከር ጭምር ሆስፒታሎችን ደረጃ በደረጃ ለመገንባት እንሰራለን" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የሠራዊቱ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ገልጸው፣ ይህን ታሳቢ ያደረገ ከፍተኛ ግንባታ ማካሄድ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።


 

የመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ እንዳሉት ከ774 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነቡ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ የክፍለ ጦሮች መኖሪያ አምስት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ዛሬ ተመርቀዋል።

"አንዱ የክፍለ ጦር ካምፕ በራስ የገንዘብ አቅም የተሰራ ነው" ያሉት የዋና መምሪያ አዛዡ፣ ቀሪዎቹ ሀብት በማፈላለግ የተገነቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በአቅም ማነስ ፕሮጀክቶቹን ካጓተቱት የሥራ ተቋራጮች ጋር ውል በማቋረጥ ሥራው በራስ አቅም እንዲጠናቀቅ መደረጉንም አመልክተዋል።

"ከእዚህ በተጨማሪ የአምስቱ ካምፖች 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ዙሪያ አጥርና የኤሌክትሪክ ሥራ ሙሉ በሙሉ በራሳችን መሀንዲሶች አቅም የተከናወነ ነው" ብለዋል። 

ዛሬ የመሠረተ ድንጋይ የተቀመጠለት ሆስፒታል በ18 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚያርፍ ጠቁመው፣ ይህም ለሠራዊቱ ደረጃውን የጠበቀና የተሟላ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ለግንባታ ሥራው ሰፊ መሬት በመስጠት ትብብር ላደረገው ለኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ምስጋና ያቀረቡት ሌተናል ጄኔራል ደስታ፣ የግንባታ ሥራው በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።


 

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አበባው ሠይፈ በበኩላቸው ቀደም ሲል በኮማንዶና አየር ወለድ እዝ በቋሚነት የሠራዊት የመኖሪያ ካምፕ አለመኖሩ ሠራዊቱ በሰላም ጊዜ የተረጋጋ ማህበራዊ ኑሮ እንዳይኖረው ተግዳሮት ሆኖ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን የተጀመረው የካምፕ ግንባታ ተስፋ ሰጪ ከመሆኑም በላይ የሠራዊቱን ችግር ለመፍታት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር በሀገር መከላከያ ሠራዊት የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ የተከናወነለት የኦል ገሪማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትም በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተመርቆ ለአካባቢው ማህበረሰብ የማስረከብ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

 

 

 

  

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም