ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው- የአፍሪካ የአረንጓዴ ለውጥ ጥምረት

አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዝ በመሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የአፍሪካ የአረንጓዴ ለውጥ ጥምረት ገለጸ።

የአፍሪካ የአረንጓዴ ለውጥ ጥምረት የኢትዮጵያ ዳሬክተር ዶክተር ጥላሁን አመዴ፤ በአብዛኛው የአፍሪካ አካባቢ የተራቆተ በመሆኑ ምርትና ምርታማነትን በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ የአረንጓዴ ልማት ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ጥሩ ተስፋ የሰነቀ በመሆኑ ሁሉም ሊጋሩት የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር በምግብ እራስን ለመቻል የአፈርና የውሃ ጥበቃና እንክብካቤ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በትብብር መስራትና የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የአየር ንብረት ተጽእኖን በመከላከል የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት ለማሟላት የአረንጓዴ ልማት ላይ ቀጣይነት ያለው ስራ መስራት ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ዘላቂነት እንዲኖረው የአፍሪካ አረንጓዴ ለውጥ ጥምረት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ለምግብነት በሚውሉ የፍራፍሬ ተክሎች ላይ ትኩረት ማድረጉ በተለይም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን ዶክተር ጥላሁን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከአካባቢው ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል የግብርና ስርአት በመዘርጋት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ጥምረቱ ተመራማሪን ከአርሶ አደር እንዲሁም ፖሊሲን ከማህበረሰብ ጋር ማስተሳሰር የሚያስችል አሰራር እንዳለው አስረድተው በዚህም በአመት እስከ 30 ሚሊዮን አርሶ አደርን በመደገፍ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአፍሪካ አረንጓዴ ለውጥ ጥምረት አፍሪካን ከችግርና ለማውጣት ከ16 ዓመታት በፊት የተቋቋመ ሲሆን በአህጉሪቷ 15 አገሮች እየሰራ ይገኛል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም