በፓሪሱ "አዲስ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ " ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ዕድል የፈጠረ ነው- አቶ ማሞ ምሕረቱ - ኢዜአ አማርኛ
በፓሪሱ "አዲስ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ " ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ዕድል የፈጠረ ነው- አቶ ማሞ ምሕረቱ
አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015 (ኢዜአ) ፦በፓሪሱ "አዲስ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ " ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ዕድል የፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ተጨማሪ የፋይናንስ ኃብት ማሰባሰብን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ረገድ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በንቃት የተሳተፈችበት ጉባዔ ነበር ብለዋል።
የፓሪስ የፋይናንስ ጉባዔ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል፣ የዓለም የገንዘብ ተቋማት ማሻሻያና የታዳጊ ሀገራት ዕዳ ቅነሳ የጉባዔው ዋነኛ አጀንዳዎች ነበሩ ብለዋል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ።
የሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪክ ድርጅቶች በታደሙበት ጉባዔ ጥልቅ ውይይቶችና ምክክሮች መደረጋቸውንም አንስተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተመራው ልዑክ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ታሳቢ ባደረጉ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ በጉባዔው ከመሳተፍ ባሻገር በርካታ የጎንዮሽ ምክክሮች መደረጋቸውን አንስተዋል።
ለአብነትም ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ማሻሻያ አኳያ በተለይም ለታዳጊ ሀገሮች የሚሰጥ ካፒታል እንዲጨምር፣ የሚሰጡ ብድሮችም ከወለድ ነፃ መሆን አለበት የሚል አቋም ኢትዮጵያ ማንጸባረቋን ገልፀዋል።
በዕዳ ቅነሳ እና ሽግሽግ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ የዕዳ አመራር እንዲኖር በኢትዮጵያ በኩል ሀሳብ መነሳቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገሮች ለልማት ማሳለጫ የወሰዱት ብድር በወረርሽኝ፣ በጦርነት፣ በአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ተደራራቢ ቀውሶች በመፈተኑ የዕዳ ማስተካከያ እንዲደረግ መጠየቁን ገልፀዋል።
የዓለም ባንክን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ዋና ዓላማቸው የድህነት ቅነሳ በመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በሌሎችም ችግሮች የተፈተነውን የአገራት ኢኮኖሚ ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ እንደሚያሻ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
ኢትዮጵያም ልማቷን ለማስቀጠልና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንዲቻል ኃብት የማሰባሰብ ሥራ ያከናወነችበት ጉባዔ መሆኑን ገልፀዋል።
አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ተሞክሮዋን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማቅረቧንም አቶ ማሞ ገልፀዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ተጨማሪ የፋይናንስ ኃብት ማሰባሰብን ጨምሮ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በንቃት የተሳተፈችበት የተሳካ ጉባዔ ነበር ብለዋል።
በጉባዔው ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።
በፓሪሱ "አዲስ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ " ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የአፍሪካ አገራትን የፋይናንስ ፍላጎት ለሟሟላት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአሠራር ማሻሻያ ማድረግ አለባቸው ማለታቸው ይታወሳል።