የጂቡቲ መንግስት የሀገሪቱን የፖሊስ የክብር ኒሻን ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ሸለመ - ኢዜአ አማርኛ
የጂቡቲ መንግስት የሀገሪቱን የፖሊስ የክብር ኒሻን ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ሸለመ
አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015(ኢዜአ)፦ የጂቡቲ መንግስት የሀገሪቱን የፖሊስ የክብር ኒሻን ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዝዳንት ሸልሟል።
ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዝዳንት የክብር ኒሻን ሽልማቱ የተበረከተው በ46ኛው ዓመት የጅቡቲ ብሄራዊ ፖሊስ የምስረታ በዓል ቀን ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ የፖሊስ የክብር ኒሻኑን ከጅቡቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልቃድር ካሚል መሀመድ እጅ ተቀብለዋል።
ሽልማቱ የጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ዑመር ጊሌ በወሰኑት መሰረት የተበረከተ ሲሆን ኮሚሽነር ጀነራል ለሽልማቱ የበቁት የኢትዮ-ጂቡቲ ድንበር ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በተለይም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ በመከላከል አመርቂ ውጤት በመገኘቱ መሆኑም ተጠቁሟል።
በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተፈጠረ ያለው የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነትና ትብብር በማጠናከር በቀጣናው ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ ላበረከቱት አስተዋፆ ጭምር መሆኑም ታውቋል።
የኢትዮዽያ ፌዴራል ፖሊስ የጀመረው ሪፎርም እያመጣ ላለው ለውጥ ለጎረቤት ሀገራትም እንደ ተምሳሌት የሚወሰድና በተለያዩ የአቅም ግንባታ ተግባራት እየተደረገ ያለው እገዛ ከፍተኛ በመሆኑ ሽልማቱ መሰጠቱ ተገልጿል።
ኮሚሽነር ጀነራሉ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርሱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በጅቡቲ ብሄራዊ ፖሊስ የተሰጠው የፖሊስ የክብር ኒሻን ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለተቋሙ የተሰጠ ሽልማት መሆኑን መግለጻቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዝዳንት አክለውም ለኢትዮጵያ ፖሊስ አመራሮችና አባላት በሙሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።