ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከአገር አልፎ ለቀጣናዊ የልማት ትስስር፣ ሰላምና መረጋጋት የላቀ ጠቀሜታ አለው-ምሁራን


አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከአገር አልፎ ለቀጣናዊ የልማት ትስስር፣ ሰላምና መረጋጋት የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ  አሳሳቢነትና የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ አገር አቀፍ የፓናል ውይይት አካሂዷል።


 

ውይይቱ "የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን በአረንጓዴ አሻራ እንከላከል" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተካሄደው።

በቀጣናው ሰላምና ደኅንነት ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ያለውን ተጽዕኖ በሚመለከት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።


 

የአየር ንብረት ለውጥ ለሰው ልጅ አሳሳቢነቱ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ቢመጣም በተመራማሪዎች ደረጃ መፍትሔ ያልተገኘለት ችግር ሆኖ መቀጠሉን አንስተዋል።

በአየር ንብረት ተጽዕኖ ምክንያት የውሃ ኃብት መቀነስ፣ ድህነት፣ መፈናቀል፣ ጎርፍ፣ ድርቅ፣ ግጭትና ሌሎችም ውስብስብ ችግሮች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ለመፍትሔው የጋራ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ጥረቶችን ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከአገር አልፎ ለቀጣናዊ የልማት ትስስር፣ ሰላምና መረጋጋት የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ፕሮፌሰር  ያዕቆብ አብራርተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ወሰን አልባ በመሆኑ በዓለም፣ በአህጉርና በቀጣናው ጭምር የተጀመሩ የልማት ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር አዳነች ያሬድ፤ ኢትዮጵያ ለሰው ልጆች ሰላም፣ ደኅንነትና መረጋጋት ፈተና እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የጀመረችው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በቀጣናውም ይሁን አጠቃላይ በአህጉር ደረጃ ጥሩ መነቃቃት የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የውሃ መጠንን በመጨመር፣ ሥርዓተ-ምኅዳርን በማስጠበቅ፣ የአፈር ለምነትን በመጨመር፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና ሌሎች አዎንታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ችግሩን መቋቋምና መከላከል ይገባል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ፤ የመገናኛ ብዙኃን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሥራት አለባቸው ብለዋል።


 

የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ለተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና እንክብካቤ ትኩረት በመስጠት በዘላቂነት ማሳወቅና ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም