የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ከአገር አስተማማኝ ዘብነቱ ባለፈ በአፍሪካ በዘመናዊነቱ የሚጠቀስ ተቋም ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው- ብርጋዴር ጄነራል ነገራ ሌሊሳ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ከአገር አስተማማኝ ዘብነቱ ባለፈ በአፍሪካ በዘመናዊነቱ የሚጠቀስ ተቋም ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው- ብርጋዴር ጄነራል ነገራ ሌሊሳ
አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015 (ኢዜአ): የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ከአገር አስተማማኝ ዘብነቱ ባለፈ በአፍሪካ በዘመናዊነቱ የሚጠቀስ ተቋም ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአቪየሽንና ኤር ሎጂስቲክስ ብርጋዴር ጄነራል ነገራ ሌሊሳ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ኮሚሽን ሰብሳቢ ሰላማዊት ዳዊትና በክልሎች ደረጃ የሚገኙ የኮሚሽኑ አመራሮች የአየር ኃይሉን የለውጥ ሥራዎች ጎብኝተዋል።
ለጎብኝዎቹ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአቪየሽንና ኤር ሎጂስቲክስ ብርጋዴር ጄነራል ነገራ ሌሊሳ፤ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የአየር ኃይሉ ቁመና ኢትዮጵያን የማይመጥን ደረጃ ላይ ነበር ብለዋል።
በውድ ዋጋ የተገዙ አውሮፕላኖች ያለአገልግሎት የተቀመጡበትና ጠንካራ አደረጃጀት ያልነበረው ተቋም ሆኖ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
ከለውጡ በኋላ ግን አየር ኃይሉ ብቁ የሰው ኃይልና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተላበሰ በማድረግ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተሰርቷል ብለዋል።
በዚህም አየር ኃይሉን የኢትዮጵያ አስተማማኝ ዘብ በማድረግ መገንባት መቻሉን ገልጸው፤ ያለአገልግሎት ቆመው የነበሩ አውሮፕላኖችን በመጠገንና በማሻሻልም ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ከአገር አስተማማኝ ዘብነቱ ባለፈ በአፍሪካ በዘመናዊነቱ የሚጠቀስ ጠንካራ ተቋም ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ብርጋዴር ጄነራሉ ገልፀዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ሰብሳቢ ሰላማዊት ዳዊት፤ መንግሥት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ላይ ያካሄደውን ተጨባጭ ለውጥ በኢትዮጵያ አየር ኃይል መመልከታቸውን ተናግረዋል።
አየር ኃይሉ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ ከማስከበር ባለፈ ከየትኛውም አካል የሚሰነዘርን ትንኮሳ አስቀድሞ መመከት የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑን አይተናልም ብለዋል።
በአየር ኃይሉ የተመዘገቡ ለውጦችን በሌሎች ተቋማት ለመድገምና የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ያለንን የሰው ኃብትና ቁሳቁስ በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባም ተምረናል ነው ያሉት።
ሌሎች የክልልና የዞን የኮሚሽኑ አመራሮች በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የኢትዮጵያውያን ኩራትና መከታ መሆኑን በማየታችን ተደስተናል ብለዋል።
አየር ኃይሉ በሰው ኃይል የተጠናከረና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የተገነባ በመሆኑም ኩራት ተሰምቶናል ነው ያሉት።
በአየር ኃይሉ አውሮፕላኖችን በራስ አቅም የመጠገንና የማሻሻል ሥራ ፈጠራና ፍጥነት የታከለበት በመሆኑ ሁላችንም እንድንማርበት አድርጎናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ጨምሮ ሌሎቹንም የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት በማዘመን ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተመሠረተ 94 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በጠንካራ አደረጃጀቱና በዘመናዊነቱ የአሁኑ ቁመናው የላቀ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል።