ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ቦትስዋና የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽንን ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ 


አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ እና ቦትስዋና የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽንን ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ሙክታር ከድር(ፒ ኤች ዲ) ከቦትስዋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ዳይሬክተር ፑሌ ምፖትዌ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ የሁለትዮሽ እና የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽንን ማጠናከር ጨምሮ በሌሎች የባለ ብዙ ወገን የትብብር መድረኮች በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።

የጋራ ኮሚሽኑ መጠናከር የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሻሻል እና ለማጎልበት ቁልፍ መሆኑ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

ኢትዮጵያ እና ቦትስዋና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1999 ነው።

ቦትስዋና በአዲስ አበባ ኤምባሲ ያላት ሲሆን ኢትዮጵያም ፕሪቶሪያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ከቦትስዋና ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን እያከናወነች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም