በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራው ምርጫ ታዛቢ ልዑክ በሴራሊዮን እየተካሄደ ያለውን አጠቃላይ ምርጫ እየታዘበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራው ምርጫ ታዛቢ ልዑክ በሴራሊዮን እየተካሄደ ያለውን አጠቃላይ ምርጫ እየታዘበ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015(ኢዜአ)፦ በቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራው የአፍሪካ ሕብረት የአጭር ጊዜ ምርጫ ታዛቢ ልዑክ በሴራሊዮን እየተካሄደ ያለውን አጠቃላይ ምርጫ እየታዘበ ይገኛል።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሴራሊዮን አጠቃላይ ምርጫ ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ በመካሄድ ላይ ነው።
ሴራሊዮናውያንም አዲስ ፕሬዝዳንት እና መንግስት መምረጥ የሚያስችላቸውን ድምጽ እየሰጡ ይገኛሉ።
ድምጽ ለመስጠት ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መመዝገባቸውን የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ገልጿል።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው የወቅቱ የሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮን ጨምሮ 13 እጩዎች ተሳትፈዋል።
በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራው የአፍሪካ ሕብረት የአጭር ጊዜ ምርጫ ታዛቢ ልዑክም የምርጫውን ሂደት በመታዘብ ላይ ነው።
በተጨማሪም የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ(ኢክዋስ) እና ሌሎች ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የምርጫውን ሂደት እየታዘቡ ይገኛሉ።