ቀጥታ፡

ለዘንድሮው የሐጅ ስነ- ስርአት ከ11 ሺህ በላይ ሑጃጆች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዘዋል - የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት

 አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015(ኢዜአ) ለዘንድሮው የሐጅ  ስነ- ስርአት ከ11 ሺህ በላይ ሑጃጆች ወደ ሳዑዲ አረቢያ መጓዛቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለፀ።

በእስልምና ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ሥፍራ ከሚሰጣቸው ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች አንዱ የሐጅ ጉዞ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም ከተለያዩ የዓለም አገራት በየዓመቱ የእምነቱ ተከታዮች ለሐጅና ዑምራ ሥርዓት ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚያመሩ ይሆናል።


 

ለዚሁ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በየዓመቱ ወደ ሥፍራው በማቅናት ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን ይወጣሉ። 

በመሆኑም ከኢትዮጵያ ለዘንድሮው የ1 ሺህ 444 ዓመተ-ሒጅራ የሐጅ ጉዞ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም በመጀመሪያው ዙር በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል 387 ሑጃጆችን በመሸኘት መጀመሩ ይታወሳል።


 

የጉዞ ሂደቱ በተለያዩ ዙሮች ቀጥሎ በዘንድሮው የሐጅ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከ11 ሺህ በላይ ምዕመናን ወደ ሥፍራው መሸኘታቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅና የሐጅ ኮሚቴ አባል ሸኽ አብዱልአዚዝ አሎ፤ ለዘንድሮው የሐጅ ሥነ-ሥርዓት ትናንት ምሽት 200 ሑጃጆችን በመሸኘት የጉዞ ሂደቱ ተጠናቋል ብለዋል፡፡  

ለዘንድሮው የሐጅ ጉዞ መሳለጥ በ18 የመመዝገቢያ ማዕከሎች በበይነ-መረብ በመመዝገብ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መሰጠቱን አስታውሰው፤ ከ11 ሺህ በላይ ሑጃጆች መጓዛቸውን ገልፀዋል።

አምና ለዚሁ ተመሳሳይ ተግባር 4 ሺህ ሑጃጆች ብቻ መጓዛቸውን አስታውሰው፤ የዘንድሮው ጥሩ አፈጻጸም የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ ጉዞ መሳካት በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እና ባንኮች የነበራቸውን ቀና ትብብር በማድነቅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ለሐጅ ተጓዦች በሙሉ መልካም ምኞታቸውን ገልፀው፤ የአረፋ በዓልን ሕዝበ ሙስሊሙ በሰላምና በመረዳዳት ከሌሎች የእምነቱ ተከታዮች ጋር በአብሮነት እንዲያሳልፍ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሑጃጆችን ጉዞ የተሳካ ለማድረግ በተደረገው ጥረት ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ወቅትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የመልስ ጉዞው ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም