ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በቅጡ በመረዳት የተባበረና የተጠናከረ የዲፕሎማሲ ጥረት ማድረግ ይገባል--  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

 አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ  በመረዳት የተጠናከረ የዲፕሎማሲ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ አምባሳደሮች፣ የቀድሞ አምባሳደሮች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የዓለም የዲፕሎማሲ ጉዞ ፈተና የበዛበት መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አንፃር ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት ከጊዜው ጋር የሚራመድ ስልትና አሰራር መከተል አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም የአሁኑ መድረክ የ2016 ዓ.ም የዲፕሎማሲ እቅድን ለማውጣትና ቀጣይ ስራዎችን ለማከናወን ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በቅጡ በመረዳት የተባበረና የተጠናከረ የዲፕሎማሲ ጥረት ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።

በዓለም ተገማች ያልሆኑ፣ ተለዋዋጭ ፍላጎቶችና አሰላለፎች መኖራቸውን  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። 

በመሆኑም ዲፕሎማሲን በብቃት፣ በጥበብና በጥንቃቄ መምራት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ለዚህም ዝግጁ የሆነ ዲፕሎማትና ባለሙያ አስፈላጊ በመሆኑ ኢትዮጵያ በትክክለኛው ቦታ እና ወቅት ላይ እንድትራመድ በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።

የዲፕሎማሲ ስራ ለብሔራዊ ጥቅም በመቆም በቁርጠኝነት መስራትን የሚጠይቅ በመሆኑ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመገንዘብ የትብብር ፖሊሲን መሰረት በማድረግ መንቀሳቀስ  ይገባል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም