ቀጥታ፡

የሀገራዊ ምክክሩ የተሳታፊ ልየታና አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት አካታችና ገለልተኛነቱን ጠብቆ እየተካሄደ መሆኑን አረጋግጠናል-የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015  (ኢዜአ):- የሀገራዊ ምክክሩ የተሳታፊ ልየታና አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት አካታችና ገለልተኛነቱን ጠብቆ እየተካሄደ መሆኑን ማረጋገጡን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ መድረኮችን የማመቻቸት ኃላፊነት ይዞ እየሰራ ይገኛል።

በቀጣይ ዓመት ለሚካሄደው ብሔራዊ የምክክር መድረክም የዝግጅት ስራዎች እየተካሄዱ ሲሆን በተለይ የተሳታፊ ልየታና አጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎች በተለያዩ ክልሎች እየተከናወኑ መሆኑ ይታወቃል።

የዝግጅት ስራው አካታች፣ ገለልተኛና ተዓማኒ ሆነው እንዲካሄዱ በየወረዳው ትብብር የሚያደርጉና የሚታዘቡ ሰባት ተባባሪ አካላት የተለዩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አንዱ ነው።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ፤ የጋራ ምክር ቤቱ የተሳታፊዎች ልየታ ሂደትን ለመታዘብ በየወረዳው አንድ ተወካይ በመመደብ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የእስካሁኑ ሂደትም በመልካም ሁኔታ መቀጠሉን ጠቅሰው በሂደቱ የሚነሱ ጉድለቶች ሲያጋጥሙም ለምክክር ኮሚሽኑ እያቀረብን ነው ብለዋል።

ሀገሪቱ ካለችበት የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮች አኳያ ምክክሩ በተረጋጋና በጥንቃቄ እንዲካሄድ እናግዛለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በኮሚሽኑ አማካሪ ቡድንና በተባባሪነት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በዚህም የምክክር ሂደቱ ከዝግጅት እስከ ፍጻሜው ድረስ አካታችና ገለልተኛ ሆኖ እንደሚሰራ አረጋግጠው፤ በአሁኑ ወቅት ከ40 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብረው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በራሳቸው ምክንያት እስካሁን በይፋ ከኮሚሽኑ ጋር ተቀራርበው መስራት ያልጀመሩ ከ10 በላይ ፓርቲዎች እንዳሉ ጠቅሰው ለሁሉም ፓርቲዎች በተሳታፊ ልየታና በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ በደብዳቤ ጠይቋል ብለዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ የመላ የኢትዮጵያውያንን የምክክር መድረክ የሚያመቻች በመሆኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራሮች ጋር አጀንዳዎቻቸውን እንዲያቀርቡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ፤ ኮከስ በሚል ቡድን የተደራጁ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀደም ሲል ከሀገራዊ ምክክሩ እንወጣለን የሚል ቅሬታ እንደነበራቸው አስታውስዋል።

ምክር ቤቱ እነዚህን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር ለማቀራረብ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት አብሮ የመስራት ተስፋ ሰጪ ነገሮች አሉ ብለዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ እንዲረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ለመወሰን  ሀገራዊ ምክክሩ የተሻለ አማራጭ በመሆኑ አካታችነቱና ገለልተኛነቱ በተረጋገጠ መንገድ እንዲካሄድ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባቶች ላይ በአካታች ሀገራዊ ምክክር በማካሄድ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት፣ ገለልተኛ የሆነ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 መቋቋሙ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም