ቀጥታ፡

በሞጆ ከተማ የቱሉ ጭሪ ተራራን ባለፉት አራት ዓመታት በማልማት ጥብቅ ደን ማድረግ መቻሉ ተገለፀ

 አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015(ኢዜአ)  በሞጆ ደረቅ ወደብ ተርሚናል አስተባባሪነት ላለፉት አራት ዓመታት የአረንጓዴ ልማት የተከናወነበትን የቱሉ ጭሪ ተራራን ጥብቅ ደን ማድረግ መቻሉ ተገለፀ።  

የተራራው መልማት ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ በቀጣይም ለንብ ማነብ፣ ለመዝናኛና ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ምቹ ሥፍራ ለማድረግ መታቀዱ ታውቋል።

በሞጆ ከተማ የቱሉ ጭሪ ተራራ የሞጆ ደረቅ ወደብ በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ ከ62 ሺህ በላይ የፍራፍሬ ተክሎችና አገር በቀል ችግኞች ተተክለው ከ85 በመቶው በላይ ጸድቀዋል።

በአካባቢው ቀደም ሲልም በርካታ የእጽዋት ዝርያዎች የነበሩ በመሆኑ እነርሱን በመንከባከብና ተጨማሪ ዛፎችን በመትከል ጥብቅ ደን ማድረግ መቻሉን በሞጆ ደረቅ ወደብ የሰው ኃብት አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ገቢታ ራጎ በተለይ ለኢዜአ ገልፀዋል።

በቱሉ ጭሪ ተራራ 14 ነጥብ 5 ሄክታሩን አገር በቀል እፅዋቶችን በማልበስ የአካባቢውን ሥነ-ምኅዳር በመጠበቅ የተዋበ ሥፍራ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በሞጆ ደረቅ ወደብ አማካኝነት የደን ጥበቃና እንክብካቤ የሚያደርጉ 28 ወጣቶች በቋሚነት ተቀጥረው በመሥራታቸው የተሳካ ልማት ማከናወን ተችሏል ብለዋል።


 

የወደቡ ከፍተኛ ኦፊሰር  ጉልላት መለሰ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ባሕርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ በአካባቢ ጥበቃ ሥራ የካበተ ልምድ ያለው መሆኑን ገልጸው፤ በሥሩ የሚተዳደረው የሞጆ ደረቅ ወደብም ተመሳሳይ ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይ የቱሉ ጭሪ ተራራን ለንብ ማነብ፣ ለመዝናኛና ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ የተመቸ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።

በዚህ ዓመትም በአካባቢው ተጨማሪ ቦታ በመረከብ 20 ሺህ አገር በቀል ችግኞችን ለመትከል ተዘጋጅተናል ብለዋል።


 

ከጥብቅ ደኑ ጠባቂዎችና ተንከባካቢዎች መካከል አቶ ደመቀ ተሰማ፤ አካባቢው ቀደም ሲል የተራቆተና ቆሻሻ የሚጣልበት እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ በመልማቱ ምቹና ማራኪ ሥፍራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተፈጠረው የሥራ ዕድልም እሳቸውና ሌሎችም የአካባቢው ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም