ቀጥታ፡

በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስባቸውን የፋይናንስ ጉድለት መሙላት ይገባል--ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ


አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015(ኢዜአ)፦በ27ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በተገባው ቃል መሰረት በማደግ ላይ ያሉ ሃገራትን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚደርስባቸው ጉዳት የፋይናንስ ድጋፉን በመስጠት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

“ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ሆናለች፤ በዚህም እየተከሰተ ያለው ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥና ድርቅ የምግብ እና የውሃ ሀብት ዋስትና እንዳይረጋገጥ ምክንያት ሆኗል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመልዕክታቸው።

ይህም በዜጎች እና አገራዊ ልማቱ ላይ ቀጥተኛ ስጋት ደቅኗል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ጠቁመዋል።

ለእነዚህ ፈተናዎች መፍትሔ ለመስጠትም በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ክፍተት መሙላት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

28ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን የምታስተናግደው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በሚመለከታቸው አካላት እና በሀገራት መካከል መግባባትን በመፍጠር ከጉባኤው ተጨባጭ ውጤት እንደምታስገኝ ሙሉ እምነት እንዳላቸውም ነው የጠቆሙት።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ሱልጣን አል ጃብር በአየር ንብረት ለውጥ ዲፕሎማሲ፣ የመንግስት አስተዳደር እና የንግድ ዘርፍ ልምድ እንዳላቸው እና የዓለም የፋይናንስ ስርዓት መቀየር እንዳለበት የሚረዱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ይህም በዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት በማምጣት ዜጎች እና የምንኖርባትን ምድርን ለመደገፍ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ዶክተር ሱልጣን አል ጃብር በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የታዳሽ ኃይል ኩባንያ “Masdar” ሊቀ-መንበርነታቸው በኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት የአገሪቱ ንጹህ ኃይል አቅም ለማሳደግ እያደረጉት ላለው ድጋፍም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም