የመከላከያ ሚኒስቴር ለሚያስገነባው የደቡብ ግንባር የሠራዊት ሆስፒታል የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሚኒስቴር ለሚያስገነባው የደቡብ ግንባር የሠራዊት ሆስፒታል የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
ሀዋሳ ሰኔ 17/2015(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በ4 ቢሊዮን ብር ወጪ ለሚያስገነባው የደቡብ ግንባር የሠራዊት ሆስፒታል በኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
በቢሻን ጉራቻ ከተማ አካባቢ ለሚገነባው ሆስፒታል የመሰረት ድንጋይ ለማስቀመጥ በተዘጋጀ ሥነ-ስርአት ላይ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተገኝተዋል።
የሆስፒታሉ ግንባታ በ17 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን የግንባታ ሥራውም በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።
ከመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ በተጨማሪ በመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ያስገነባቸው የክፍለ ጦርና የሻለቃ መኖሪያ ካምፕና ቢሮዎች ምረቃ መርሃ ግብርም ተካሂዷል።
በተጨማሪም በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር በሀገር መከላከያ ሠራዊት የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ የተከናወነለት የኦል ገሪማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተመርቆ ለአካባቢው ማህበረሰብ የማስረከብ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው።