ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከሞዛምቢክ ጋር በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መድረኮች ያላትን ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ዝግጁ ናት-አምባሳደር ሽብሩ ማሞ 

 

አዲስ አበባ ሰኔ 17/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሞዛምቢክ ጋር በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መድረኮች ያላትን ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ዝግጁ መሆኗን አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ገለጹ።

ሁለቱ አገራት በተለያዩ መስኮች የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ  እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል።

በታንዛኒያ፣ ማላዊና ሞዛምቢክ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑን አምባሳደር ሽብሩ ማሞ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ፍሊፕ ንዩሲ አቅርበዋል።

አምባሳደር ሽብሩ የሹመት ደብዳቤያቸውን ባቀረቡበት ወቅት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ሁለቱ አገራት ሊተባበሩ በሚችሉባቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።

“ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮቿን በአፍሪካ ማዕቀፍ ስር ለመፍታት ያሳየችው ፅናት፤ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለው መርህ በሁሉም በኩል ከተተገበረ ለአህጉሪቱ ውስጣዊ ችግሮች መፍትሄ እንደሚያመጣ ሁነኛ ማሳያ ነው” ብለዋል አምባሳደሩ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከድህነት ለማላቀቅ እና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለማግኘት የምትገነባው የልማት ፕሮጀክት መሆኑን አመልክተዋል።

የግድቡ ግንባታው በመላ ኢትዮጵያውያን ንቁ ተሳትፎ የሚገነባ ብሔራዊ አርማ በመሆኑ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናውና ለአፍሪካ የኩራት ምንጭ ነው ሲሉም ገልጸዋል። 

ሁለቱ አገራት በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መድረኮች ያላቸውን ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ኢትዮጵያ ዝግጁ እንደሆነች ጠቁመዋል።

የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ፍሊፕ ንዩሲ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ውስጣዊ ችግሮችን ለመፍታት በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ስምምነት ለመተግበር ያሳየው ቁርጠኛ አቋም የሚደነቅ ነው ብለዋል። 

“አፍሪካውያን ከምንግዜውም በላይ በትብብር የምንሰራበት ጊዜ አሁን ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ አሁን እያካሄደች ካለው ልማት አገራቸው ብዙ ልምድ እንደምትወስድ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ከዚህ በፊት ሁለቱ አገሮች ከተፈራረሟቸው ስምምነቶች መካከል እስካሁን የተተገበረው የአየር አገልግሎቱ ብቻ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ የተቀሩትን ፈጥኖ መተግበር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ መከላከል እንደሚገባ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም