ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያዊያን ለአንድ አላማ በጋራ እንዲሰለፉ ያደረገ የልማት አሻራ ነው--አቶ አደም ፋራህ

ባህር ዳር፣ሰኔ 16/2015 (ኢዜአ)  “የአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር ኢትዮጵያዊያንን ለአንድ አላማ እንዲሰለፉ ያደረገ ታላቅ የልማት አሻራ ነው" ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

በአማራ ክልል የ2ኛው ምእራፍ የመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት የፌዴራልና የክልል ባለስልጠናት በተገኙበት በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ጎሃ ቀበሌ ዛሬ ተከናውኗል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክልት እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄ እየተተገበረ ይገኛል።

መርሃ ግብሩ በመላው የአገራችን አካባቢዎች የሚካሄድ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያንን ለአንድ አላማ ያሰለፈ  የልማት አሻራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህም ልክ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ የአንድነት መንፈስና ተነሳሽነት የታየበት በመሆኑ የብልጽግናን መሰረት ለማጽናት የሚያስችል ነው ብለዋል።

''የተገኘው ድልም እኛ ኢትዮጵያዊያን ለሀገርና ለህዝብ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ሁሉም ሊተገብረው ይገባል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል አመራርና ህዝብ የመጀመሪያውን ምእራፍ የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ማሳካቱን ጠቁመው በ2ኛው ዙርም እንደ ሃገር 25 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ለማሳካት የበኩላቸውን ሚና መጫወት አለባቸው ብለዋል።


 

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትልቅ ስኬት የታየበት ስራ ነው ብለዋል።

''ህዝብን በማስተባበርና በማሳመን መስራት ከተቻለ የማይሳካ ነገር የለም'' ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ይህም የ2ኛውን ምእራፍ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ እስከ ቀበሌ በንቅናቄ በመምራት ይከናወናል።

በድርቅ ምክንያት በተደጋጋሚ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስና ምርታማነትን ማሳደግ የሚቻለው የአረንጓዴ አሻራን መርሃ ግብር በመተግበር መሆኑን በመገንዘብ አመራሩና ህዝቡ በቅንጅት መስራት አለበት ብለዋል።

ህዝቡ ከአመራሩ ጋር በመቀናጀት የመጀመሪያውን ምእራፍ የአረንጓዴ አሻራ በድል እንዳጠናቀቀው ሁሉ 2ኛውንም መድገም አለበት ያሉት ደግሞ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ ናቸው።


 

በመጀመሪያው ምእራፍ 25 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል የአፈር መሸርሸርን በማስቀረትና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ጠቁመው ይህም ለአለም ምሳሌ የሆነ ውጤት ነው።

በ2ኛው ምእራፍ  የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር በደን፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በመኖ ምርትና ሌሎች ጥምር የእርሻ አመራረት ላይ በማተኮር የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል።


 

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማሪያም ከፍያለው እንደገለጹት በክልሉ በመጀመሪያው ምእራፍ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል።

በመጀመሪያው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ከ700 ሽህ ሄክታር በላይ መሬት መሸፈን የተቻለ ሲሆን የጽድቀት መጠኑም 77 በመቶ  መሆኑን አረጋግጠዋ።

የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ መቀመርም ሃምሌ 01/2015 ዓ.ም በአንድ ጀምበር የሚተከለውን 260 ሚሊዮን ችግኝ ጨምሮ በዘንድሮው መርሃ ግብር ብቻ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በመረሃ-ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና ወረዳ ከፍተኛ አመራሮችንና የአካባቢው ህብረተሰብ መሳተፋቸው ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም