ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥ አካታች ልማትን በማረጋገጥ ሰላምን ለማጽናት የተያዙ የዘላቂ የልማት ግብ አጀንዳዎችን ለማሳካት ጫና ፈጥሯል-  ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም 

አዲስ አበባ ሰኔ 16/2015(ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥ አካታች ልማትን በማረጋገጥ ሰላምን ለማጽናት የተያዙ የዘላቂ የልማት ግብ አጀንዳዎችን ለማሳካት ጫና መፍጠሩን የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ  አሳሳቢነትና የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ አገር አቀፍ የፓናል ውይይት ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል አካሄዷል።

የፓናል ውይይት "የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን በአረንጓዴ አሻራ እንከላከል" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከናወነው።

በዚሁ ጊዜ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተላቸው ካሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መካከል የሕዝብ ሰላምና ደህንነትን ላይ ተጽእኖ መፍጠር አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብት እና ፖለቲካ ቀውሶችን በማስከተል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በማህበረሰብ ሰላምና ደህንንት ላይ እያሳደረ ያለው ተጽእኖ አንገብጋቢ ሆኗል ብለዋል።


 

በዚህም ድርቅ፣ መፈናቀል፣ በአገራት መካካል የተፈጥሮ ሃብት ግጭትን በማስከተል በማህበረሰብ ዘንድ ሰላምና ደህንነት እንዲደፈርስ ምክንያት እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት አቶ ብናልፍ።

ይህም የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ የተካተቱ ሰላምን ማጽናት እና አካታች የማህበረሰብ ልማት አጀንዳዎችን ለማሳካት ጫና መፍጠሩን ገልጸዋል።

በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ እያሳደረ ያለውን ተጽእኖ ለመቀነስ የራሳቸውን መርሐ-ግብር ቀርጸው መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አመታት ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል ተጽእኖውን ለመቋቋምና በችግሩ ምክንያት የሚከሰተውን የሰላም እና ደህንነት ስጋት ለመቀነስ እየሰራች ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።

በመድረኩ የአየር ንብረት ለውጥ  በቀጣናው ሰላምና ደህንንት ላይ ባለው ተጽእኖ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም በሚኖረው ሚና እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመቀነስ  በሚኖራቸው ሚና ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በፓናል ውይይቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ዓለም አቀፍ የልማትና የምርምር ተቋማት፣የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ተወካዮችና ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም