የኮሚሽኑ ስራ ውጤታማ እንዲሆን የህዝቡ ተሳትፎና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-ዶክተር አይሮሪት መሐመድ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሚሽኑ ስራ ውጤታማ እንዲሆን የህዝቡ ተሳትፎና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-ዶክተር አይሮሪት መሐመድ
ቦንጋ ሰኔ 16 / 2015 (ኢዜአ)፦ የኮሚሽኑ ስራ ውጤታማ እንዲሆን የህዝቡ ተሳትፎና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አይሮሪት መሐመድ ገለጹ።´
ኮሚሽነር አይሮሪት ለኢዜአ እንደገለጹት ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ባሉ ሂደቶች ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎና እየሰጠ ያለው እገዛ የሚደነቅ ነው።
የህብረተሰቡ ተሳትፎ ለኮሚሽኑ ጉልበት እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፤ እስካሁን ባሉ ሂደቶች ከቀበሌ ጀምሮ ህብረተሰብ እየፈፀመ ያለው ተግባር ለኮሚሽኑ የወደፊት ጉዞ መልካም መደላድልን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ በኮሚሽነሮችና በጥቂት አካላት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ የሲቪክ ማህበራት ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል፣ በንቃት በመሳተፍና ኮሚሽኑን በመደገፍ ለውጤታማነቱ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
እንደ ኮሚሽነሯ ገለፃ ህብረተሰቡ ያለማንም ግፊትና ተፅዕኖ በራሱ ተነሳሽነት ኮሚሽኑ በሚያዘጋጃቸው የውይይት መድረኮች ላይ በመሳተፍ ለኮሚሽኑ ተግባር የሚረዱ ጠቃሚ ሀሳቦችን እያነሳ ነው።
የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት ህዝቡ በመሆኑ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በሀገራዊ ምክክሩ በግልፅና በፍትሃዊነት የማሳተፉ ስራ በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነር ዶክተር አይሮሪት ተናግረዋል።
የኮሚሽኑን ተልዕኮ ከዳር እንዲደርስ ህብረተሰቡ በከፍተኛ ተነሳሽነትና መነቃቃት ከኮሚሽኑ ጎን ሆኖ እገዛ እያደረገ መሆኑን እስካሁን ባሉት ሂደቶች መገንዘብ ችለናልም ብለዋል።
ዶክተር አይሮሪት እስካሁን ያለው የህብረተሰቡ ተሳትፎና ድጋፍ የኮሚሽኑ ስራ ግቡን እንደሚመታ ማሳያ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እያካሄደ ያለው የአጀንዳ ልየታ መርሃ ግብር ስኬታማ መሆኑንም አመልክተዋል።