ቀጥታ፡

የድሬዳዋ የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች ማህበር  አባላት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቁ

ድሬዳዋ ሰኔ 16/2015 (ኢዜአ) የድሬዳዋ የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች እያበረከቱ ያለውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ጠየቁ።

የድሬዳዋ የሌሊት የታክሲ አሽከርካሪዎች ማህበር አባላት "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ  የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ደም በመለገስ ጀምረዋል።

ከንቲባ ከድር በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የማህበሩ አባላት የድሬዳዋ ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ ለማስቀጠል ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እያበረከቱ የሚገኙት ሥራዎች በአርአያነት የሚጠቀስ ነው።

አባላቱ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል፣ ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡና አቅመ ደካማ አዛውንቶችን ቤቶች ለማደስና በደም እጥረት የዜጎች ህይወት እንዳያልፍ እያበረከቱ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ የሚመሰገንና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ገልጸዋል።
 

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው፤ የማህበሩ አባላት የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በየሶስት ወራቱ እያበረከቱት የሚገኙት ደም ልገሳ በደም እጥረት የሚከሰት ሞት እየታደገ ይገኛል ብለዋል።

ደም መለገስ በጤና ላይ የሚያስከትለው አንዳችም ችግር እንደሌለ አመልክተው፣ኅብረተሰቡ ደም በመለገስ የወገኖቹን ሕይወት በመታደግ ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል ።
 

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ የማህበሩ አባላት ከፀጥታ አካላት ጋር ሌት ተቀን ተቀናጅተው የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ እያከናወኑ የሚገኙት ሥራ በአርአያነት የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ጤናዬ ደምሴ በበኩላቸው  የማህበሩ አባላትና የፖሊስ አባላት ህይወትን ለመታደግ በቋሚነት እየለገሱ የሚገኙት ደም በደም ዕጥረት፣ በድንገተኛ አደጋና በወሊድ ጊዜ የሚከሰትን ሞት እንደሚያስቀር ተናግረዋል።

እንደ አገር ባለፉት 11 የበጀት ወራት በመላው አገሪቱ ከበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች 320ሺህ ዩኒት ደም ውስጥ የድሬዳዋ አስተዳደር ያበረከተው ድርሻ የሚያበረታታ እንደነበር ገልጸዋል።

የድሬዳዋ የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች ማህበር አባል ወጣት ሄኖክ አደለ፤ የማህበሩ አባላት የአገርን ከፍታ ዕውን ለማድረግና የአካባቢውን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያከናውኑትን የበጎ ፈቃድ ስራዎች እንደሚያጠክሩ ገልጿል።

የጤና ችግር የማያስከትለውን ደም መለገስ የህሊና ደስታ ይሰጣል ብሏል።

በዚሁ ወቅት የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ከ27 እስከ 35 ጊዜያት በቋሚነት ደም ለለገሱ ነዋሪዎች ዕውቅና፣ የምስክር ወረቀትና ዋንጫ አበርክቷል።

ዋንጫ ከተበረከተላቸው ሰዎች መካከል 35 ጊዜ ደም የለገሱት የጤና ባለሙያ አቶ አቤል አለምሰገድ ደም በመለገስ የዜጋን ህይወት ማዳን የመሰለ የሚያስደስትና የሚያረካ ነገር እንደሌለ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

የድሬዳዋ የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች ማህበር 500 አባላት ያሉትና በ2012 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን፣ ማህበሩ በልማት፣ በሰላምና በፀጥታ ዘርፍ እያከናወነ ባለው አርአያነት ያለው እንቅስቃሴ በሰላም ሚኒስቴር ዕውቅና አግኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም