ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከዜና ምንጭነቱ ባሻገር

አፍሪካ በአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ስር ወድቃ ጨለማ ውስጥ በነበረችበት ወቅት በ1934 ዓ.ም “አዣንስ ዳይሬክሲዮን’ በሚል ስያሜ አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በወቅቱ አጠራር በጽህፈት ሚኒስቴር ስር እንደ አንድ የስራ ክፍል ሆኖ መረጃን ተደራሽ የማድረግ አላማ ይዞ ተቋቋመ።

በጊዜው ለነበሩት ሬዲዮ ጣቢያ እና ጋዜጦች ልዩ ልዩ ዘገባዎችን አጠናክሮ በማቅረብ የሚታወቀው የዛሬው የኢዜአ  ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡ 32 አገራትን ይዞ ከተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በ21 ዓመታት ይቀድማል።

በ1957 ዓ.ም ስያሜው በቀዳማዊ  አፄ ኃይለ ስላሴ አማካኝነት “ አዣንስ ዳይሬክሲዮን ወደ “የኢትዮጵያ የወሬ ምንጭ” ተቀየረ።

በ1960 ዓ.ም ደግሞ ራሱን ችሎ በመውጣት “የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት” በመባል በአዋጅ ተቋቋመ።

ኢዜአ ላለፉት 80 ዓመታት ብቸኛው የኢትዮጵያ የዜና ምንጭ በመሆን እያገለገለ በርካታ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈ አንጋፋ የሚዲያ ተቋም ነው።

ድርጅቱ ከቀድሞው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ስር ወጥቶ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ ራሱን ከቻለ በኋላ ትልቅ አገራዊ ተልዕኮ ይዞ ዳግም በአዋጅ ተቋቁሟል።

በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ የመሆን ራዕይ የሰነቀው ኢዜአ፤ በአገልግሎቱ ሁለንተናዊ የለውጥ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

በአገራዊ ገጽታ ግንባታ፣ በብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ መግባባትና በሌሎች ዘርፈ ብዙ ሕዝባዊ አጀንዳዎች ላይ በስፋትና በጥራት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የ10 ዓመታት ፍኖተ ካርታም አዘጋጅቷል።

ኢዜአ በዜናና ዜና ነክ፣ በፎቶና በዘጋቢ ፊልም፣ በሕትመት፣ በስልጠናና ማማከር ስራዎች ተደራሽነቱን እያሰፋ ይገኛል።

ከፍኖተ ካርታው ዕቅዶች መካከል የራሱ የብሮድካስት አገልግሎት ለመጀመር የታቀደ ሲሆን ፤ ለዚህም በማቋቋሚያ አዋጁ ሕጋዊ መሰረትና መንግስታዊ ድጋፍ አግኝቷል።

ድርጅቱ 3 ዘመናዊ የቴሌቪዥንና 4 የሬዲዮ ስቱዲዮዎች ግንባታ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑንና አስፈላጊ ግብዓቶች በማሟላት በቀጣይ ዓመታት ውስጥ ወደ ብሮድካስት አገልግሎት ለመግባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአገር ውስጥ 38 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ፣ የእንግሊዝኛ፣ የፈረንሳይኛ እና አረብኛ ቋንቋዎችን እየተጠቀመ ይገኛል።

በዚህ ዓመትም ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በአረብኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች በቻናል ለመውጣት እየተዘጋጀ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ መረጃዎችን በፈረንሳይኛና ትግሪኛ ቋንቋዎች ተደራሽ የሚያደርግ አዲስ ድረ-ገጽም አስጀምሯል።

ከአጀንዳው ቀረጻ በተጨማሪም ኢዜአ ለተለያዩ የፌደራል እና የክልል ተቋማት በሚዲያና ኮሚኒኬሽን የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

ተቋሙ ስልጠና ከመስጠት ባሻገር ከተለያዩ ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን በመስራት ላይ ነው።

ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጠባቸው የሚገኙ የተለያዩ በጎ ተግባራትንም እያከናወነ ይገኛል።

ኢዜአ ከዜና ምንጭነቱ ባሻገር ወደ ብሮድካስት አገልግሎት መግባቱ በአገር ውስጥና በውጭ የመረጃ ተደራሽነትን ለማስፋት ብሎም አገራዊ ገጽታ ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ላይ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችለው አቅም እንደሚፈጥርለት ይታመናል።

የአገርን ገጽታ የሚገነቡ፣ የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድሙና ብሔራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በጥራት መስራት የሚያስችለውን ሪፎርም እያካሄደ ይገኛል።

በሪፎርም ስራው እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት አንዱ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ አጀንዳ በመቅረጽ የፖሊሲ አውጪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ የሚያስችል ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

ኢዜአ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ከፍ የሚያደርግ የገጽታ ግንባታ እንዲሁም ኢትዮጵያ እያለፈችበት የምትገኘውን ለውጥ ለማጽናት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሕዝብ ትክክለኛ የሆነ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው።

ሕብረ-ብሔራዊ በሆነችው ኢትዮጵያ ኢዜአ በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች ካሉት ሰፊ ተደራሽነት አኳያ መረጃዎች በተጠናከረና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ወደ ሕብረተሰቡ የማድረስ ስራን በማከናወን ላይ ይገኛል።


 

በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር "መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ ጥቅም" በሚል መሪ ሃሳብ መጋቢት 29 2015 ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ይጠቀሳል።

በምክክር መድረኩም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በምክክር መድረኩ የመገናኛ ብዙሃን ለአገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር፣ ለዴሞክራሲና ሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና በሚመለከት የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው ነበር።

በሌላ በኩልም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት እና ኦቪድ ግሩፕ ጋር በመተባበር "አዲስ አበባን በአዲስ የዲፕሎማሲ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ ግንቦት 1 2015 አካሄዶ ነበር።

በምክክር መድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም፣ የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ፤ እንዲሁም ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የታሪክ ምሁራን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ ዲፕሎማቶች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ አዲስ አበባ ከተማን ከዲፕሎማሲ፣ ከመሰረተ ልማት፣ ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከለውጥ ስራዎችና ቀጣይ አቅጣጫን መሰረት ያደረጉ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።

በ2015 በጀት ዓመት ኢዜአ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ የውይይት መድረጎችን አዘጋጅቷል።

የዛሬው የፓናል ውይይትም ኢዜአ እያከናወነች ያለው የአጀንዳ ቀረጻ ስራዎች አካል ነው።

በውይይቱ መክፈቻ ላይ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም፣የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የቦርድ አባል እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፣ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ተቋማት እና ምሁራን፣የዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በውይይቱ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ በመነሳት የአየር ንብረት ለውጥ እያሳደረ ያለውን ተጽእኖ ላይ የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚመላከቱበት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ለቀጣናዊ ሰላም እና ደህንነት እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ባለድርሻ አካላት ባሻገር የማህበረሰቡና የመገናኛ ብዙሃን ሚናን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሆች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም