ቀጥታ፡

በሀይቆቹ  ህገወጥ ማስገርን ለመከላከል በተከናወነ ስራ ለገበያ የቀረበ የአሳ ምርት ጨምሯል-መምሪያው 

አርባ ምንጭ ሰኔ 16/2015 (ኢዜአ) በዓባያና ጫሞ ሐይቆች ላይ የሚፈጸም ህገወጥ ማስገርን ለመከላከል በተከናወነ ስራ ለገበያ የቀረበ የአሳ ምርት መጨመሩን  የጋሞ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ 11 ወራት 4 ሺህ 175 ቶን የዓሣ ምርት ለአካባቢና ማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን መምሪያው ገልጿል።

የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም ዛፉ ለኢዜአ እንደገለጹት የዓባያና ጫሞ ሐይቆች ባላቸው ከፍተኛ የዓሣ ሀብት እንደ ሀገር የሚታወቁ ናቸው።

"ይሁን እንጂ በሐይቆቹ ላይ በሚፈጸም ሕገ-ወጥ ማስገርና የአመራረት ችግር በሐብቱ ላይ ጉዳት ሲደርስ ቆይቷል" ብለዋል።

ህገወጥ አሰጋገሩ ያልተፈቀደና ጉዳት ያለውን መረብ በመጠቀም የሚፈጸም መሆኑ ደግሞ ከሀይቆቹ ለምግብነት ያልደረሰ ጫጩት ዓሣ ያለገደብ በማውጣት ለሀብቱ መመናመንና ለዝርያ መጥፋት አደጋዎች እንዲጋለጡ ማድረጉን አመልክተዋል ።
 

የዞኑ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ከመከረ በኋላ መምሪያውን ጭምር በአባልነት ያካተተ ግብረ ኃይል በማደራጀት በሀይቆቹ ላይ የሚፈጸም ህገወጥ ተግባር የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

በሀይቆቹ ላይ የሚፈጸም ህገወጥ ማስገርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተከናወነ ስራ ያልደረሱ የዓሣ ጫጩቶችን በመያዝ በሀብቱና በዝርያዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትል የነበረን “ሞኖፕላመንት” የተሰኘ 31 ሺህ 823 መረቦች ተሰብስበው እንዲቃጠሉ መደረጉን አመልክተዋል።

በሕገ-ወጥ መንገድ ያሰግሩ የነበሩ ግለሰቦችን ወደ ህጋዊ መስመር ማስያዝም ሌላኛው ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ከ20 በላይ ህገ-ወጥ አስጋሪዎች ሕጋዊ ሆነው ተደራጅተው እንዲሰሩ በመደረጉ በሀይቆቹ የአሳ ምርት እንዲጨምር አስተዋፅኦ ማድረጉን  ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

በዚሁ መሰረት በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ከሐይቆቹ 4 ሺህ 242 ቶን አሳ ለማምረት ታቅዶ 4 ሺህ 175 ቶን ዓሣ ለአካባቢና ለማእከላዊ ገበያ መቅረቡን ኃላፊዋ ተናግረዋል።

የገበያ ሰንሰለት በመፍጠር ከምርቱ 50 በመቶ ለአካባቢ ገበያ እንዲሁም 50 በመቶ ደግሞ ለማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ መደረጉን ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

ከሀይቆቹ በወራቶቹ ተመርቶ ለገበያ የቀረበው አሳ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ53 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ጠቁመው "ለውጤቱም በሀይቆቹ ላይ የሚፈጸም ህገወጥ ማስገርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተከናወነ ስራ የአሳ ሀብት እየጨመረ መምጣቱ ዋናው ምክንያት ነው" ብለዋል ።

በዞኑ በዓሣ ማስገር ሥራ የተሰማሩ 32 ህጋዊ ማህበራት መኖራቸውን ጠቅሰው ምርቱን በማከፋፈል ተግባር የተሰማሩ በርካታ ነጋዴዎች መኖራቸውንም አመልክተዋል።
 

የአርባ ምንጭ ዓሣ አስጋሪዎች ስፔሻላይዝድ መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ዳዊት ደጾ በበኩላቸው በዞኑ ህገ-ወጥ ዓሣ አስጋሪዎችን ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በሀይቆቹ የአሳ ሀብት እየጨመረ እንዲመጣ ከማድረግ ባለፈ ከ10 ዓመታት በፊት የጠፉ የዓሣ ዝርያዎች እየተገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ዘንድሮ ካለፈው ዓመት የበለጠ ምርት እየተገኘ ነው " ያሉት ሊቀመንበሩ ማህበሩ ባለፉት 11 ወራት 2 ሺህ 20 ኩንታል ዓሣ ለገበያ በማቅረብ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በሀይቆቹ ጠፍቶ የነበረና በአካባቢው "ባርበስ" በመባል የሚታወቅ የአሳ ዝርያ ወደ ምርት መመለሱን አመልክተዋል።
 

ማህበራቸው ህጋዊ በመሆኑ አባላቱ በሚያገኙት ገቢ ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የሌቶ ዓሣ አስጋሪዎች ማህበር አባል አቶ ዳርሶ ደረሰ ናቸው።

በሚያገኙት ገቢ ሰባት የቤተሰብ አባላትን እያስተዳደሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ማህበሩ ህገ-ወጥ መረብ ይዞ በተገኘ አባል ላይ የ5 ሺህ ብር ቅጣትና ከማህበሩ ለስድስት ወራት የሚያገል ህገ ደንብ አውጥቶ ተግባራዊ በማድረግ ህገ ወጥነትን ለመቆጣጠር የድርሻውን እየተወጣ መሆኑንአመልክተዋል።

የጫሞ ሐይቅ 4 ሺህ 500 ቶን፣ የዓባያ ሐይቅ ደግሞ 600 ቶን ዓሣ በዓመት የማምረት አቅም እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም