ከሰዎች ዕይታ አድማስ ተሸሽጎ የቆየው የአቤ ሐይቅ ተስፋ - ኢዜአ አማርኛ
ከሰዎች ዕይታ አድማስ ተሸሽጎ የቆየው የአቤ ሐይቅ ተስፋ

አዲስ አበባ ሰኔ16/2015 (ኢዜአ) የአዋሽ ወንዝ ድንበር ሳያቋርጥ፣ ባይተዋርነት ሳይሰማው፣ ወረት ሳያሻፍረው፣ እንደ ግዮን ግንድ ብቻ ይዞ ሳይዞር...የእናት ሀገሩን ደጃፍ ቃኝቶ፣ ቁጣና ሐሴቱ፣ ጥማትና ድሎቱን በግልፅ ተናግሮ ከመሸበት ያድራል።
በምዕራብ ሸዋ ቆፈን የተፀነሰው አዋሽ ከሸዋ ተረተሮች ፋፍቶ፣ በጉራጌ ጅረቶችና በአርሲ ወንዞች ጎልምሶ፣ በአፋር ምድረ በዳዎች አመሻሽቶ፣ በሀሩር እቶን ተኮራምቶ ከኢትዮጵያ ሳይሻገር ዳር አገር ላይ ይሞታል።
የአዋሽ ወንዝ መጨረሻ መዳረሻው፣ የፍላሚንጎዎቹ መንሳፈፊያው፣ የበርሐ ሲሳይ የሆኑ ቴምርና መሰል ተክሎች የከበቡት አቤ ሐይቅ፣ የቆላማ ብዝሐ ሕይወት መሰረት፣ የአርብቶ አደሮችም ጌጥ እና ሕይወት ነው።
ሐይቁ በሰንሰለት የተቆራኙ ስድስት ሐይቆችን ያቀፈ ሲሆን አጠቃላይ 336 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው።
መልከ ብዙው አቤ ሐይቅ፤ ተደራሽ ካልሆኑ የምድራችን አካባቢዎች አንዱ ቢሆንም አሁን ለጎብኚዎች ዕይታ ሊበቃ፣ ለሀገር ኢኮኖሚ ጌጥና ዋልታ ሊሆን የተቃረበ ይመስላል።
ከቀደምት የሐውሳ ሱልጣኖች መናገሻ ከሆነችው አይሳኢታ ከተማ በቅርብ ርቅት ላይ የሚገኘው አቤ ሐይቅ፤ አሁን ላይ ሐይቁን ተንተርሶ ወደ ጅቡቲ የሚወስድ ኮንክሪት አስፓልት መንገድ እየተገነባ መሆኑ ለተደበቀው አቤ ሐይቅ ጸጋ እሴት ጨምሮ ለመጠቀም ትልቅ ዕድል ፈጥራል።
በአፋምቦ ወረዳ ከአቤ ሐይቅ ዳር የተወለዱት ወጣት መሀመድ አሊ እና አቶ ሳዲ ኩማር ወደ ጅቡቲ የሚያስወጣው መንገድ ግንባታ ለአካባቢው ቱሪዝም ልማት ትልቅ ተስፋ መሆኑን ይናገራሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው ከሚገኙ ስደተኞች ጋር በመሆን በሐይቁ አሳ በማስገር ቤተቦቻቸውን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ወደፊትም በተሻለ ደረጃ ተጠቃሚ ለመሆን ትልቅ ህልም እንዳላቸው ነው የተናገሩት።
በአይሳኢታ የስደተኞች ጣቢያ አስተባባሪው አብዱራዛቅ ሙሳ በበኩሉ አቤ ሐይቅና አካባቢው ለዕይታ ተጋርዶ የቆየ መሆኑን በመጥቀስ ይህ ታሪክ የሚሆንበት ጊዜ መቃረቡን ነው የሚገልጸው።
ሀይቁ እምቅ የቱሪዝም አቅም ያለው በመሆኑ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለሌሎችም የሚተርፍ መሆኑን ይናገራል።
የአይሳኢታ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀቢብ አሊ፤ ከሰመራ በአይሳኢታ ወደ ጅቡቲ የሚወስደው መንገድ መጀመሩ ለአይሳኢታ ከተማና አካባቢው ልማት መነቃቃት ትልቅ ተስፋ የሰጠ በመሆኑ በጉጉት እየተጠበቀ ነው ብለዋል።
መንገዱ ለወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራና ንግድ ስራ መቀላጠፍ ትልቅ ዕድል እንዳለው ገልጸው፤ ባለሀብቶችም በአካባቢው መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
አይሳኢታ በእሳተ ጎመራ ከተከበበው አቤ ሐይቅ በቅርብ ርቀት ከመገኘቷ ባሻገር ለቱሪስት መስህብ የሚሆን የሱልጣን አሊሚራህ ሃንፈሬ ቤተ-መንግስትም በአካባቢው ይገኛል።