ቀጥታ፡

የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በተሻለ ውጤት ለማለፍ የሚያስችል ዝግጅት አድርገናል--የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተፈታኝ ተማሪዎች

ደሴ ሰኔ 16/2015 (ኢዜአ) ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠውን የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና በተሻለ ውጤት ለማለፍ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተፈታኝ ተማሪዎች ገለጹ።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ በራሱ፣ በግል ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሩ ከ8ሺህ በላይ ተማሪዎችን የመውጫ ፈተና ለመፈተን የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን አስታውቋል።

በዩኒቨርሲቲው የትምህርት እቅድና ሥራ አመራር ትምህርት ከፍል ተማሪ ፉዓድ ሱነሞ ለኢዜአ እንደገለጸው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና በላቀ ውጤት ለማለፍ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግሯል። 

ቀደም ሲል የተማርኩትን በማጥናትና በመከለስ ካደረኩት ዝግጅት በተጨማሪ በመምህራን የተሰጣቸውን የማካካሻ ትምህርት በአግባቡ መከታተሉንም ገልጿል።

የመውጫ ፈተናው ተማሪው የጨበጠውን እውቀት የሚገመግምበትና እንደሀገርም የተሻለ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ በመሆኑ መቀጠል እንዳለበት ገልጿል።

"እኔም በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ያገኘሁትን እውቀት ለመፈተሽ ፈተናው በእጅጉ ያግዘኛል" ያለው ተማሪ ፉዓድ፣ በቀጣይ ለሚሰማሩበት የሙያ መስክ ብቁ ሆነው እንዲወጡ አጋዥ መሆኑንም ተናግሯል።

በዩኒቨርሲቲው የማናጅመንት ተማሪ የሆነችው መካ ዋሴ በበኩሏ በሰጠችው አስተያየት እንዳለቸው የመውጫ ፈተናው ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ጠንክረው እንዲማሩና እንዲያጠኑ የሚያነሳሳ ነው።

"በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚሰጠውን ፈተና ለማለፍ በቂ ዝግጅትና ልምምድ አድርገናል" ያለችው ተማሪ መካ ፣ በመምህራን ከተሰጣቸው የማካካሻ ትምህርት በተጨማሪ የተለያዩ መጻህፍትን በማንበብ ሲዘጋጁ መቆየታቸውን ገልጻለች።

"የመውጫ ፈተናው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ተማሪዎች በራሳቸው ጥራት በቅተው እንዲወጡ ለማድረግና እንደሀገር የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት ያግዛል" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት እቅድና ሥራ አመራር መምህር አቶ ጀማል ይማም ናቸው።

የዘንድሮ ተፈታኝ ተማሪዎች ብቁ ሆነው እንዲወጡና በፈተናው የላቀ ውጤት እንዲያመጡ በበይነ መረብ ጭምር የታገዘ ተደጋጋሚ ፈተና በመስጠት የማዘጋጀትና የማለማመድ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ፈተናው የሚዘጋጀው በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከተማሩት ትምህርት በመሆኑ ተማሪዎች ውጤታማ ለመሆን ፈተናውን ተረጋግተው መፈተን እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃን አስማሜ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሰጠው የመውጫ ፈተና የግል ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ጨምሮ ከ8ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመፈተን የዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ተፈታኝ ተማሪዎች መካከል ከ2ሺህ 580 በላይ የሚሆኑት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች  መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ፈተናው በበይነ መረብ የሚሰጥ በመሆኑ ተማሪዎች በቂ ልምምድና ዝግጅት አድርገዋል" ያሉት ዶክተር ብርሀን፣ በፈተና ወቅት የኤሌክትሪክ ሃይል መቋረጥና መሰል ችግሮች ቢከሰቱ ፈጥኖ ለመፍታት በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና እንደ ሀገር መሰጠቱ ተማሪዎች እውቀታቸውን እንዲያዳብሩና የተማሩትን ከልሰው እንዲያነቡ ከማድረግ ባለፈ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም