ቀጥታ፡

በመቀሌና አክሱም ከተማ የሚገኙ የደም ባንኮች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ገብተዋል-የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት

አዲስ አበባ ሰኔ 16/2015(ኢዜአ)፦ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በመቀሌና አክሱም ከተሞች የሚገኙ የደም ባንኮች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ መግባታቸውን የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሐብታሙ ታዬ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ 43 የደም ባንኮች መካከል ሦስቱ በትግራይ ክልል እንደሚገኙ ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡


 

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የደም ባንኮቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡

በተለይ በደም ባንኮቹ አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎች ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር ያሉባቸውን የግብዓት ችግር መቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎች ስለመከናወናቸው አብራርተዋል፡፡

በዚህም በአክሱምና መቀሌ የሚገኙ የደም ባንኮች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም የመቀሌ የደም ባንክ 8 ሺህ እንዲሁም የአክሱም የደም ባንክ 6 ሺህ ዩኒት ደም በማሰባሰብ አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ደምና ቲሹ ባንኩ በዋናነት የደም ማሰባሰብ ሥራውን ከበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች ጋር በትብብር በማከናወን የተሰበሰበውን ደም ጥራት የማስጠበቅ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ 

በዚህም ጥራቱን ጠብቆ እንዲቀመጥ የተደረገውን ደም ለሚያስፈልጋቸው ሰዎችና አገልግሎቱን ለሚሰጡ ተቋማት በማሠራጨት ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

አገልግሎቱ በዘንድሮው የክረምት መርሃ-ግብር በሦስት ወራት ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ 108 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ያቀደ ሲሆን ፤ ከዚህም ውስጥ 37 ሺህ ዩኒት የሚሆነውን ደም በአዲስ አበባ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡

ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሃ-ግብር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት።

ሕብረተሰቡ መጪውን የክረምት ወቅት በበጎ ፈቃድ ደም በመለገስ ወገናዊ አለኝታነቱን በተግባር እንዲያሳይም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም