የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በብሔራዊ መግባባት እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እያከናወነ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በብሔራዊ መግባባት እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እያከናወነ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በብሔራዊ መግባባት እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የሚያከናውነውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ የቦርድ አባል እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት “የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖዎችን በአረንጓዴ አሻራ መዋጋት” በሚል መሪ ሀሳብ በጋራ ያዘጋጁት በአየር ንብረት ለውጥ እና በአረንጓዴ አሻራ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል እየተካሄደ ነው።
በፓናሉ ላይ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የቦርድ አባል እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ተቋማት እና ምሁራን እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ እና በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ የተቋሙ የቦርድ አባል እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገልጸዋል።
ከዜና ምንጭነቱ ባሻገር በብሔራዊ መግባባት እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነም ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በቀጣናዊ ሰላም እና ደህንነት ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ አስመልክቶ የተዘጋጀው የፓናል ውይይት የዚሁ አጀንዳ መፍጠር አካል መሆኑን አመልክተዋል።
ውይይቱ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመከላከል የሚያስችሉ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ የጋራ መፍትሔ ማበጀት የሚያስችል አማራጭ እንደሚፈጥር ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ ያስረዱት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በብሔራዊ መግባባት እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ በየዓመቱ በቋሚነት የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት መታቀዱንም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በውሃ፣ በግብርና በአጠቃላይ በተፈጥሮ ሀብት ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ ዘርዝረዋል።
በዚህም ምክንያት የምግብ እጥረትና ሌሎች ችግሮችን እያስከተለ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ጫና ለመቋቋም በአለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖን ለመቋቋም የወጡ መርሐ-ግብሮችን ጨምሮ በራሷ የተለያዩ ማዕቀፎችን በመቅረጽ ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ከእነዚህም መካከል የአረንጓዴ አሻራ፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ የግብርና ስራዎች፣ የመስኖ ልማትና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የመቋቋም ጉዳይ የሁሉም ድርሻ በመሆኑ መገናኛ ብዙሀን ግንዛቤ በመፍጠር፣ ፓሊሲዎችን በማስተዋወቅና በሌሎች ተግባራት ስራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ዶክተር ማንደፍሮ ጠይቀዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፓለቲካ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ በሚኖረው ተጽዕኖ ላይ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በጽሁፋቸውም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ አለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታውን በመቃኘት ጎርፍ፣ ስደት፣ ግጭት እያስከተላቸው ከሚገኙ የተጽዕኖ ውጤቶች መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።
በተመሳሳይ በምጣኔ ሀብት፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በጂኦፓለቲካዊና ሌሎች ዘርፎች ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና በመዘርዘር መፍትሔዎቻቸውንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ባዘጋጁት እና በአየር ንብረት ተጽዕኖና መፍትሄዎቻቸው ላይ ትኩረት አድርጎ እየተካሄደ በሚገኘው የፓናል ውይይት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም እና የመገናኛ ብዙሃን ሚና የአየር ንብረት ተጽእኖን ለመቀነስ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበዋል።