የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል እና ሰላምን ለማስፈን ወሳኝነት አለው- አቶ ብናልፍ አንዷለም - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል እና ሰላምን ለማስፈን ወሳኝነት አለው- አቶ ብናልፍ አንዷለም
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2015(ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከሰቱ ችግሮች ለመከላከል እና ሰላምን ለማስፈን ያለው ሚና ቁልፍ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።
የአየር ንብረት ለውጥ እና አረንጓዴ አሻራ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ውይይቱ እየተከናወነ የሚገኘው “የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖዎችን በአረንጓዴ አሻራ መዋጋት” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
በውይይቱ መክፈቻ ላይ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የቦርድ አባል እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ተቋማት እና ምሁራን፣ የዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የሕዝቦችን ሰላም እና ደህንነት እየተፈታተኑ ለሚገኙ በርካታ ችግሮች መከሰት መንስኤ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ በዋናነት እንደሚጠቀስ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጡ ሰላማዊ የሆነ ሁሉን አቀፍ የማህበረሰብ ልማትን ለማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂ የልማት ግቦች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይሳኩ ዋና ማነቆ ሆኖ መቀጠሉን አመልክተዋል።
ይህም በሰው ልጆች ኑሮ፣ ሰላምና ደህነነት ላይ የሚያስከትለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰው በችግሩ ሳቢያ የእርሻ ቦታዎች ወደ በረሃማነት የመለወጥ፣ ድርቅ እና ሌሎች ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ፈጥሯል ብለዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰተው ቀውስ እየሰፋ ሲመጣ የአገራት የውስጥ ሰላምና ጸጥታቸው እንዲናጋ እንዲሁም ከሌሎች አገራት ጋር ወደ ግጭት እንዲገቡ የሚያደርጉ ክስተቶች መፈጠራቸው የማይቀር መሆኑንም ገልጸዋል።
ይህም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለከባቢያዊ ሰላም እና ደህንነት መጠበቅ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት በየዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር እየተካሄደ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በመርሐ-ግብሩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን የመትከልና የማጽደቅ ተግባርን ጨምሮ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ነው የሰላም ሚኒስትሩ ያብራሩት።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እያከናወነች ባለው ተግባር አረንጓዴ ልማትን በማረጋገጥ ብልጽግናን እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም የውስጥ ሰላምን የሚጎዱ፣ ለግጭት በር የሚከፍቱና በተፈጥሮ ሀብት ሽሚያ የሚከሰቱ ተግባራትን በማስወገድ ኢትዮጵያ ለቀጣናው የሚተርፉ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን አስረድተዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያሉትን ችግሮች መፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ለሌሎች የቀጣናው አገራት ምሳሌ የሚሆን ተግባር እያከናወነች መሆኑንም ነው አቶ ብናልፍ ያነሱት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አሳሳቢ በሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በትብብር ላዘጋጁት ጠቃሚ የውይይት መድረክ የሰላም ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ተቋማቱ በሌሎች አብይ አገራዊ ጉዳዮች ላይም ተመሳሳይ የውይይት መድረኮች የማዘጋጀት ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።