ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ኩዌት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ይበልጥ ተቀራርበው መስራት አለባቸው -አምባሳደር ሰይድ ሙሐመድ 


አዲስ አበባ ሰኔ 16/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያንና የኩዌትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ አገራቱ ይበልጥ ተቀራርበው መስራት እንደሚገባቸው በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሰይድ ሙሐመድ ገለጹ።

በኩዌት የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተከፈተበት 25ኛ ዓመት በኩዌት ሲቲ ተከብሯል።

በአከባበር ስነ-ስርዓቱ የኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች፣ መቀመጫቸውን በኩዌት ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የንግድ ሰዎች፣ በአገሪቱ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሰይድ ሙሐመድ ሁለቱ አገራት ስላላቸው የረጅም ጊዜ እና የባለ ብዙ ዘርፍ ግንኙነት አንስተዋል።

የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ይበልጥ ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አቅም እና የቱሪዝም መዳረሻዎችን አስመልክቶ ለኩዌት ባለሀብቶች ገለጻ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በኩዌት የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኩዌት ቢሮ መርሐ-ግብሩን በጋራ አዘጋጅተዋል።

ኢትዮጵያ እና ኩዌት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1967 ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም