የአልጄሪያው አስሚዳል ግሩፕ በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ምርት ዘርፍ ያሉ እድሎችን ለመመልከት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአልጄሪያው አስሚዳል ግሩፕ በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ምርት ዘርፍ ያሉ እድሎችን ለመመልከት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2015(ኢዜአ)፦ የአልጄሪያው አስሚዳል ግሩፕ በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ምርት ያሉ እድሎችን ለመመልከት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።
በአልጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በአልጄሪያ አናባ ከተማ ከሚገኘው የአስሚዳል ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መሐመድ ጣሃር ሄውን እና የድርጅቱ የማኔጅመንት አባላት ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፍጆታ፣በመስኩ ትብብር በማድረግ እና በኢትዮጵያ ምርት ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ገልጸዋል።
የአስሚዳል ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መሐመድ ጣሃር ሄውን ኩባንያው በተለያዩ የማዳበሪያ አይነቶች ያለውን የምርት አቅም እንዲሁም አልጄሪያ በዓለም ዋና ዋና ማዳበሪያ አምራች አገራት ተርታ ለመሰለፍ በቀረጸችው ፕሮጀክት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኩባንያው በኢትዮጵያ በማዳበሪያው ምርት ያሉ እድሎችን ለመፈተሽና በመስኩ በጋራ ለመስራትና ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
የአስሚዳል ግሩፕ እ.አ.አ 1984 የተቋቋመ ሲሆን የታዋቂው የአልጄሪያ ሶናትራክ ኩባንያ አካል ነው።
የኢንዱስትሪ ተቋሙ የማዳበሪያ እና ተባይ ማጥፊያ ምርት እና ግብይት ላይ የተሰማራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።