ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ለሀገራዊ አንድነት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት የጀመራቸውን ተግባራት ለማሳካት ኃላፊነታችንን እንወጣለን-በድሬዳዋ የኅብረተሰብ ተወካዮች

ድሬዳዋ  ሰኔ 15/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ አንድነት፣ ዘላቂ ሰላም እና ልማት እንዲረጋገጥ የሚያካሂዳቸውን መድረኮች ስኬታማ ለማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በድሬዳዋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ገለጹ።

በድሬዳዋ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በቀጣይ በሚያካሂደው ሀገራዊ የምክክር መድረክ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ወኪሎች የሚመረጡበት ሥነ ሥርዓት ዛሬ በድሬዳዋ መካሄድ ጀምሯል።

በሦስት ቀናት የምልመላ ሂደት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው በምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች ከህብረተሰቡ ከተውጣጡ ነዋሪዎች በገለልተኝነት ይመረጣሉ።

በዛሬው እለትም ከከተማ፣ ከቀበሌዎችና ገጠር ወረዳዎች ኮሚሽኑ በሚያካሂደው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ላይ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮች ምልመላ እየተካሄደ ነው።
 

በወኪሎች መረጣ ላይ የተሳተፈችው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ተማሪ ሄዋን ተፈራ እንዳለችው፤ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው በምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ሰዎችን በገለልተኝነትና በራስ ፈቃድ የተካሄደው መረጣ ወሳኝ ነው።

ሀገራዊ የምክክር መድረክ ለማካሄድ የተጀመረው ጥረት የሚበረታታና በሁሉም ዜጎች ወስጥ ተስፋ የፈነጠቀ መሆኑን ገልጻ፣ ኮሚሽኑ የሰነቀውን የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም የማረጋገጥ ራዕይ ለማሳካት ኃላፊነቷን እንደምትወጣ ተናግራለች።                 

ኮሚሽኑ የሰነቀው ተልዕኮ ስኬታማ እንዲሆን የሃይማኖት አባቶች ለአገር ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ተከታዮቻቸውን ማስተማራቸው አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት ደግሞ ሊቀ አዕላፍ ቀለመወርቅ ሙሉ ተድላ የተባሉ የከተማው የሃይማኖት አባቶች ተወካይ ናቸው።                                                      

በተወካዮች መረጣና በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የአገር ሽማግሌ አቶ ብርሃኔ ጎበና በበኩላቸው "ሀገራዊ የምክክር መድረኩ በአገር መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ለማምጣት መሠረታዊ ሚና አለው" ብለዋል።

ልዩነት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ መግባባት በመፍጠርና ቀጣዩን ዘመን ብሩህ ለማድረግ ለዘመናት ያካበቱትን ልምድ ተግባራዊ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል።

ብሔር ብሔረሰቦች ያላቸውን ፍቅርና አንድነት አፅንተው የጋራ አገራቸውን እንዲያሳድጉ የኮሚሽኑ ተልዕኮ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል'' ያሉት ደግሞ ሴቶችን በመወከል በመረጣው ሂደትና ውይይት ላይ የተሳተፉት ወይዘሮ የኋላሸት አድማሱ ናቸው።           
                                                     

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር በሰጡት ማብራሪያ በውይይቱ  የድሬዳዋን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና አደረጃጀቶች የሚወክሉ 700 ተወካዮች በነፃነትና በገለልተኝነት መመረጣቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ከእያንዳንዱ አደረጃጀት አራት፣ አራት ተወካዮች የተመረጡ ሲሆን በተጨማሪም አንድ አንድ ተጠባባቂ መመረጣቸውን ነው ያመለከቱት።

በሀገራዊ ምክክር መድረኩ ላይ እንዲሳተፉ የተመረጡት ሰዎች በቀጣይ የሚወክሉትን የህብረተሰብ ክፍል አጀንዳ በማሰባሰብ ወደፊት በሚካሄደው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ላይ እንደሚሳተፉም አምባሳደር መሐሙድ አስታውቀዋል። 

 

                                                                   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም