ቀጥታ፡

ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ከ100 ግራም በላይ ወርቅ በመኖሪያ ቤታቸው ያከማቹ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ሰኔ 15/2015(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኦሞ ዞን የጦር መሳሪያ እና ከ100 ግራም በላይ ወርቅ በመኖሪያ ቤታቸው ያከማቹ 13 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የማዕድን ግብይት አዋጅ ቁጥር 1144/2011 የተደነገገውን ክልከላ በመተላለፍ በሕገ-ወጥ መንገድ የወርቅ ማዕድን በመኖሪያ ቤታቸው በማስቀመጥ ለግል ጥቅማቸው ለማዋል ሲሉ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ከሕብረተሰቡ ባገኙት መረጃ መሰረት በመኖሪያ ቤታቸው ባደረጉት ፍተሻ መሆኑን ገልጿል።

በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤት ከ100 ግራም በላይ ወርቅ፣ ሁለት የወርቅ ማዕድን መፈለጊያ ማሽን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያን በመጣስ በቤታቸው ውስጥ የተቀመጠ ከ1 ሚሊዮን በላይ ብር፣ ሰባት ክላሺንኮቭ ጠመንጃ ከ326 መሰል ጥይቶች እና ስድስት ሽጉጥ ከ30 መሰል ጥይቶች ጋር መያዙን አመልክቷል።

የተያዙት ተጠርጣሪዎች ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ነው ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ የጠቆመው።

ሕብረተሰቡ በመሰል የወንጀል ድርጊቶች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች እና ቡድኖችን በማጋለጥ አሳልፎ ለጸጥታ አካላት በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም