በኢትዮጵያ የድንገተኛ ሕክምና አስተዳደር ሥርዓትን ለማሻሻል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የድንገተኛ ሕክምና አስተዳደር ሥርዓትን ለማሻሻል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የድንገተኛ ሕክምና አስተዳደር ሥርዓትን ለማሻሻል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የድንገተኛ ሕክምና አስተዳደር ሥርዓት ላይ ያተኮረ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የድንገተኛ ሕክምና አስተዳደር ሥርዓትን ለማጎልበት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዓለም በምታስተናግደው በርካታ የሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ክስተቶች በዜጎች ላይ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲያስተናግዱ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ክስተቶችን ምላሽ ለመስጠት የድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና አስተዳደር ሥርዓትን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለድንገተኛ ሕክምና አስተዳደር የሚያስፈልጉ የሕክምና ግብዓቶችን በማሟላትና የሕክምና ሙያተኞችን በማሰልጠን የድንገተኛ ሕክምና አስተዳደር ሥርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ሥርዓትን ለማሻሻል እያደረገ ለሚገኘው ጥረት ደጋፊዎች እገዛቸውን እንዲያስቀጥሉ ጠይቀዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ የድንገተኛ ሕክምና አስተዳደር ሥርዓት አቅሞችን ለማጎልበት እየተደረገ ያለውን ጥረት አደጋን ቀድሞ ለመቆጣጠር ያግዛል ብለዋል።
የኅብረተሰቡን ጤና አደጋ ውስጥ የሚጥሉ ክስተቶችን ቀድሞ ለመከላከልና ለመቀነስ ከግል ተቋማት ጋር ጭምር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።