ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዘላቂ የመሬት አስተዳደርና የአካባቢ ጥበቃ ላይ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች የሚደነቁ ናቸው-የአለም ባንክ


አዲስ አበባ ሰኔ 15/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዘላቂ የመሬት አስተዳደርና የአካባቢ ጥበቃ ላይ ያሳየቻቸው ለውጦችና ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች የሚደነቁ መሆናቸውን የአለም ባንክ ገለጸ።

በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ የአካባቢ፣ ተፈጥሮ ሀብትና ብሉ ኢኮኖሚ ሃላፊ ሮስ ሁዝ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ለውጦችን እያስመዘገበች መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ደግሞ በዘላቂ የመሬት አስተዳደርና የአካባቢ ጥበቃ ያሳየቻቸው ለውጦችና ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዘላቂ የመሬት አስተዳደርና የአካባቢ ጥበቃ ላይ እያከናወነች ላለው ተግባርም የዓለም ባንክ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአረንጓዴ ልማት፣ አፈር መሸርሸርን ለመከላከል፣ ማህበረሰብን ያሳተፈ የተፋሰስ ልማት፣ የእርከንና ሌሎች ስራዎች ላይ ለውጦችና አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋልም ነው ያሉት።

የአፈር ለምነትና ምርታማነትን በመጠበቅ ዘላቂ የመሬት አስተዳደር እንዲኖር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ባንኩ በቅርበት እየሰራ መሆኑም ሃላፊው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከአገር አልፎ ወደ ጎረቤት አገሮችም እየተስፋፋ መሆኑ ለዘላቂ የአካባቢ ጥበቃና የመሬት አስተዳደር ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የአረንጓዴ ልማት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ በኩልም ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት የሚተከሉ ችግኞች ዘላቂነት ላይ ትኩረት መስጠትም አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ በአካባቢ፣ በምግብ ዋስትና እና በዜጎች ህይወት ላይ ያለውን አወንታዊ ሚና በመረዳት  ሌሎች የልማት አጋሮችም ይህንኑ በጎ ዓላማ እንዲደግፉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም