ለጤናው ዘርፍ የዲጂታል ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል - የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ - ኢዜአ አማርኛ
ለጤናው ዘርፍ የዲጂታል ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል - የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2015 (ኢዜአ) በዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ለጤናው ዘርፍ የዲጂታል ግንባታ ሂደት ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ገለጹ።
በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ትብብር በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን አገር አቀፍ የጤና አውደ-ርዕይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ።
በአውደ-ርዕዩ ላይ አገራዊ የጤና ሥርዓትን በማሻሻል ሥራ ላይ ያሉ ምርትና አገልግሎቶች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን፤ ጎን ለጎንም የጤናውን ዘርፍ የሚመለከቱ የምክክር መድረኮች ተካሂደዋል።
በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን የዲጂታል ጤና እና አገልግሎት ሥርዓት መሻሻል በሚገባቸው ሥራዎች ላይ የሚመክር መድረክ በዛሬው እለት ተካሂዷል።
በመድረኩም የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ፣ የዲጂታል ጤና አማካሪዎች፣ ሙያተኞችና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ፤ በኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የዜጎችን ጤንነት በመጠበቅ ዋነኛ የልማት ተዋናይና አምራች እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም መንግሥት የዜጎችን የጤና አገልግሎት፣ ጥራት፣ ተደራሽነትና ፍላጎት ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ለጤናው ዘርፍ የዲጂታል ግንባታ ሂደት ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑንም ዶክተር እዮብ ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ፤ የዲጂታል ጤና ሥርዓትን መገንባት ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ አገልግሎትን ለማዘመን ከግልና አጋር አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዶክተር ማርቆስ ፈለቀ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ለዘርፉ እድገት መልካም አጋጣሚ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
የዲጂታል ጤና ሥርዓት የአገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት የኃብት አስተዳደርና የሚያጋጥሙ የሕክምና ስህተቶችን ለመቀነስ ጠቀሜታ እንዳለውም አንስተዋል።
በጤና ሚኒስቴር የዲጂታል ጤና ከፍተኛ አማካሪ አማኑኤል ብሩ፤ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ተለምዷዊ ዓለምን እየቀየረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ዲጂታል የጤና ሥርዓት ተደራሽነትም የዜጎችን የጤና አገልግሎት ፍላጎት በፍጥነትና በጥራት ምላሽ ለመስጠት ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ፖሊሲ፣ ፕሮቶኮል፣ የአስተዳደር ሥርዓትና የሰው ኃይል በማደራጀት እስከ ጤና ጣቢያ ድረስ ዲጂታል የጤና ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ፋሲል ኃይለማርያም፤ ኤሌክትሮኒክ ሬጉላቶሪ ሥርዓትን በመተግበር ተገልጋዮችን እያስተናገዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ተገልጋዮችም ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲገለገሉ፣ የሚፈልጉትን ጥያቄ እንዲያቀርቡና መልስ እንዲያገኙ፣ በማድረግ ምልልስና የጊዜ ብክነትን ማስቀረት እየተቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚሁ አገልግሎትም ከ20 ሺህ በላይ የምግብና መድኃኒት አስመጪ፣ አምራችና አከፋፋይ ተገልጋዮች በሚፈልጉት መንገድ እየተስተናገዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው አገር አቀፍ የጤና አውደ-ርዕይ ከትናንት ወዲያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በይፋ መከፈቱ ይታወሳል፡፡
"የቀጣዩ ትውልድ ጤና" በሚል መሪ ሃሳብ በሳይንስ ሙዚየም ለዕይታ የቀረበው አገር አቀፉ የጤና አውደ-ርዕይ ከሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን፤ በጤናው ዘርፍ የተገኙ የምርምር፣ የፈጠራ፣ ዲጂታላይዜሽንና ዘመናዊ የጤና ስኬቶች ለዕይታ ቀርበዋል።