የሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ ማራቶን ውድድር የፊታችን እሑድ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ ማራቶን ውድድር የፊታችን እሑድ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2015 (ኢዜአ) 39ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ የማራቶን ውድድር የፊታችን እሑድ በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጸ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውድድሩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ዮሐንስ እንግዳ፤ የውድድሩ ዓላማ ጀግናውን አትሌት በማስታወስ ለአትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።
በውድድሩ ለኢትዮጵያ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራትና በውድድሮች እርስ በርስ የልምድና የተሞክሮ ልውውጥ እንዲያደርጉ ነው ብለዋል።
የፌዴሬሽኑ የውድድርና ተሳትፎ የቴክኒክ ዳይሬክተር አስፋው ዳኜ በበኩላቸው፤ በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ለሚወጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁለቱም ፆታዎች አንደኛ ሆነው ለሚያጠናቅቁ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 50 ሺህ ብር፣ ሁለተኛ ለሚወጡ እያንዳንዳቸው 25 ሺህ ብር እንዲሁም ሦስተኛ ሆነው ለሚያጠናቅቁት 20 ሺህ ብር ይሰጣል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ሰሚት "ለስላሳ ፋብሪካ" ተብሎ የሚጠራው አካባቢ መነሻና መድረሻውን አድርጎ ውድድሩ የፊታችን እሑድ የሚካሄድ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህ ውድድር ከ12 ክለቦች ሁለት ክልሎችና አንድ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ በድምሩ 354 አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሏል።
የጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ የማራቶን ውድድር በ1974 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ ዘንድሮ ለ39ኛ ጊዜ ይካሄዳል።