ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥ በግብርናው ዘርፍ ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽዕኖ እና መፍትሔዎቹ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ሊካሄድ ነው

 አዲስ አበባ  ሰኔ 15/2015(ኢዜአ):-  የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽዕኖ እና መፍትሔዎቹን የሚያመላክት የፓናል ውይይት በነገው እለት በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በመተባበር ባሰናዱት መድረክ ላይ የችግሩ አሳሳቢነትና የመፍትሔ ሃሳቦች እንደሚነሱ ይጠበቃል። 
 

"የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን በአረንጓዴ አሻራ እንከላከል" በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው መድረክ በተለይም የግብርናውን ዘርፍ በእጅጉ እየፈተነ ስላለው ችግር ሰፊ ውይይት ይደረግበታል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክታዊት እጅጉ፤ የውይይት መድረኩ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዓለም ላይ እየጨመረ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ላይ እየበረታ መጥቷል ብለዋል።


 

የምርት ጥራትና የአፈር ለምነትን መቀነስ፣ የሰብል ምርትን የሚጎዱ ተባዮች መፈጠር፣ የዝናብ ወቅት መዛባት እና ሌሎችም እያደረሳቸው ካሉት ተጽዕኖዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ለዚህም በችግሩና መፍትሔዎቹ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ መካሄዱ የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም እያከናወነች ያለው ጥረትና ቀጣይ ትግበራ በሚመለከትም በመድረኩ የሚነሳ መሆኑን ጠቁመዋል።
 

የአረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ተጽዕኖን ለመከላከል እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትና በቀጣይ መከናወን ስላለባቸው ሥራዎችም እንዲሁ።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የመገናኛ ብዙኃን ሚና እና  የሚመለከታቸውን አካላት የትብብር ጥረትም በመድረኩ የሚዳሰስ መሆኑን ዳይሬክተሯ አንስተዋል።

ከአካባቢያዊ ሰላምና ደኅንነት አንጻር የአየር ንብረት ለውጥ ያለውን ተጽዕኖ በሚመለከትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ በዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ የውይይት መነሻ ጽሑፍ የሚቀርብ ይሆናል።

በፓናል ውይይቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን በግብርናው ዘርፍ የሚሰሩ አካላት እንዲሁም የልማት አጋር ድርጅቶች እንደሚገኙ ይጠበቃል።

በመድረኩ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ እያስከተለ ያለው ጉዳትና ችግሩን መቋቋም የሚያስችሉ ምክረ- ሃሳቦች በዘርፉ ምሁራን የሚነሱ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፤ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመለየት በጥናትና ምርምር ለመፍትሔው እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም