ቀጥታ፡

የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ኮሚሽን አመራሮች የኢትዮጵያ አየር ኃይል የለውጥ ስራዎችን ጎበኙ

አዲስ አበባ ሰኔ 15/2015(ኢዜአ)፦ የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ኮሚሽን አመራሮች የኢትዮጵያ አየር ኃይል የለውጥ ስራዎችን ዛሬ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ኮሚሽን ሰብሳቢ ሰላማዊት ዳዊትና በክልሎች ደረጃ የሚገኙ የኮሚሽኑ አመራሮች ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለኤር ሎጅስቲክስ ብርጋዴር ጄነራል ነገራ ለሊሳ አየር ኃይሉ መሠረታዊ ለውጥ በማካሄድ አሁን ላይ አስተማማኝ የኢትዮጵያ ዘብ መሆኑን ያስመሰከረ ተቋም መገንባቱን ገልጸዋል። 

ከተመሰረተ 94 ዓመታትን ያስቆጠረው ተቋሙ ዘመናዊ ትጥቆችን በማሟላት፣ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራትና ሰፊ መሠረተ ልማት ግንባታ ማከናዎኑን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የወጣትና አንጋፋ ተዋጊ አውሮፕላን አብራሪዎችን፣ ምርጥ ቴክኒሺያኖችንና መሐንዲሶችን እያፈራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። 

ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ያለአገልግሎት ቆመው የነበሩ አውሮፕላኖችን በመጠገንና በማሻሻል ለአየር ኃይሉ ተጨማሪ አቅም ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል። 

የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ኮሚሽን ሰብሳቢ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፤ መንግሥት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በጸጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ ያካሄደውን ተጨባጭ ለውጥ በአየር ኃይል መመልከታቸውን ተናግረዋል። 

አየር ኃይሉ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ ከማስከበር ባለፈ ከየትኛውም አካል የሚሰነዘርን ትንኮሳ አስቀድሞ መመከት የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑን አይተናል ነው ያሉት። 

ሌሎች የኮሚሽኑ አመራሮች በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የኢትዮጵያውያን መመኪያ ተቋም ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም