ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን የመምህራን ማህበር ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ - ኢዜአ አማርኛ
ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን የመምህራን ማህበር ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ

አዳማ ሰኔ 15/2015 (ኢዜአ) :-ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን የመምህራን ማህበሩና አባላቱ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ገለፁ ።
10ኛው ዓመታዊ የመምህራን ማህበር የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በኮንፈረሱ መክፈቻ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደገለጹት ኢ-ፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነት በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው።
ባለፉት ዓመታት ከትምህርት ተደራሽነትና ሽፋን አንፃር በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡ ቢሆንም ጥራት ያለውን ትምህርት ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ግን አሁንም ብዙ ሊሰሩ የሚገቡ ስራዎች አሉ ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በትምህርት ሴክተር ላይ እየተደረገ ባለው የማሻሻያ ሪፎርም ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ስርዓተ ትምህርቱን ከማሻሻል ጀምሮ በትምህርት ዕርከኖች ላይ ማሻሻያ ማድረግ፣ አዲሱን ስርዓተ ትምህርት መቅረፅና ተግባራዊ ማድረግ፣ ዩኒቨርስቲዎችን በተልዕኮና በትኩረት መለየት የመሳሰሉትን ተግባራት እንደ ማሳያ አንስተዋል።
አክለውም ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን በህብረተሰቡ ተሳትፎ በመስራት ለተማሪዎች የማብቃት ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ሳሙኤል ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነፃነት እንዲኖራቸውና ራስ ገዝ እንዲሆኑ የማድረግ ስራም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መካከል ናቸው ብለዋል።
በቅርቡ "ጥራት ያለው ትምህርት ለትውልድ የሚል ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ይጀመራል" ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፤ በዚህም በሁሉም የትምህርት ዕርከኖች ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመምህራን ማህበርና መላ አባላቱ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ኮንፈረንሱ የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ ግብዓት የሚገኝበት እንደሚሆንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ማህበሩ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።
በዚህም ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ረገድ መምህራን ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ኮንፈረንሱ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ጥራት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የመፍትሔ ሐሳቦች የያዙ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርቡበታል ብለዋል።
በዚህም በኮንፈረንሱ ላይ አምስት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው እንደሚመከርባቸው አንስተው፤ የጥናቶቹ ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች መሬት ወርዳው ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ይሰራል ብለዋል።
በማህበሩ አባላትና ምሁራን በትምህርት ጥራት ችግር አፈታት ላይ የሚቀርቡ ምክረ ሐሳቦችን ወደ ተግባር ከመለወጥ አንፃር ክፍተት መኖሩን ጠቅሰው፤ ማህበሩ የጥናት ግኝቶች ወደ ተግባር ተቀይረው ውጤት እንዲያገኙ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።
ለአንድ ቀን በተሰናዳው ኮንፍረንስ የማህበሩ አመራርና አባላት፣ መምህራንና ተጋባዥ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ታድመዋል።