የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ፋውንዴሽን የፊታችን እሁድ ስራ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ፋውንዴሽን የፊታችን እሁድ ስራ ይጀምራል
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2015(ኢዜአ):- የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ፋውንዴሽን የፊታችን እሁድ ሰኔ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ ተመስርቶ ስራ ሊጀምር መሆኑን የአርቲስቱ ቤተሰቦችና አደራጅ ኮሚቴው አስታወቁ።
የአርቲስቱ ቤተሰቦችና አደራጅ ኮሚቴው በዛሬው እለት በጋራ በሰጡት መግለጫ ፋውንዴሽኑ የአርቲስቱን ሌጋሲ ለማስቀጠል ታልሞ የሚመሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የፋውንዴሽኑ ምስረታ የምዝገባ ሂደቱ በመጠናቀቁ የፊታችን እሁድ ሰኔ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ ተመስርቶ ስራ ይጀምራል ብለዋል።
የአርቲስቱ ባለቤት ሊሊ ማርቆስ ቢራና የኮሚቴው አባል አቶ ኢፈባስ አብዱልወሀብ እንደተናገሩት ፋውንዴሽኑ በትምህርት፣ በጤና፣ በአርትና በሙዚቃ እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ይሆናል።
የክቡር ዶክተር አርቲስት ዓሊ ቢራ ከ60 ዓመታት በላይ በሰራቸው ዘመን ተሻጋሪ ድንቅ ሙዚቃዎቹ የብዙዎችን ቀልብ የገዛና በጥበብ የተሞላ ድንቅ ሰው ነበር።
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ባለውለታ ከሆኑ አንጋፋ ድምጻዊያን መካከል ዓሊ ቢራ በቀዳሚነት የሚጠቀስ መሆኑንም በመድረኩ ተገልጿል።
በተለይም ለአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው አርቲስት ዓሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም በ13 ዓመቱ “አፍረን ቀሎ” የሚባለውን ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን በመቀላቀል ነው የሙዚቃ ስራውን አንድ ብሎ የጀመረው።
ከአፍ መፍቻ ቋንቋው ከአፋን ኦሮሞ በተጨማሪ በአማርኛ፣ በአረብኛ፣ በሃረሪ እና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ድንቅ ዜማዎችን ተጫውቷል።
ከ267 በላይ ሙዚቃዎች ያበረከተው ድምጻዊው በአፋን ኦሮሞ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውን አልበሙን በ1971 ዓ.ም ከመስራቱ በተጨማሪ ለገበያ የቀረቡ 13 አልበሞች እንዳሉትም በአንድ ወቅት ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሯል፡፡
ድምጻዊ ዓሊ ቢራ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮነትና ማህበራዊ ትስስር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
በሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ መልዕክቶችን በማስተላለፍ መልካም ትውልድ እንዲቀረጽ ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።
ባለፉት 60 ዓመታት በኦሮሞ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ እንቁ ሆኖ የቆየ፣ በርካታ ወጣቶችን ማፍራት የቻለ፣ ትውልዱ በእውቀት እና በስነ-ምግባር እንዲቀረጽ በሙዚቃ ስራው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ታላቅ የሙዚቃ ሰው እንደነበረም ተነስቷል።
አርቲስቱ በዘርፉ ላበረከተው ታላቅ አስተዋፅኦ ሁለት የክብር ዶክተሬት የተሰጠው ሲሆን ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር የተለያዩ የእውቅና ሽልማቶችን አግኝቷል።
የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ባደረበት ህመም ሳቢያ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል፡፡