የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ስራዎች ከስርዓተ ምግብ ማሻሻል ጋር ተቀናጅተው እንዲተገበሩ ይሰራል -የምግብ ስርዓትና ስነ-ምግብ የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ስራዎች ከስርዓተ ምግብ ማሻሻል ጋር ተቀናጅተው እንዲተገበሩ ይሰራል -የምግብ ስርዓትና ስነ-ምግብ የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2015 (ኢዜአ) የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ስራዎች ከስርዓተ ምግብ ማሻሻል ጋር ተቀናጅተው እንዲተገበሩ የሚሰራ መሆኑን የምግብ ስርዓትና ስነ-ምግብ የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓትና ስነ-ምግብ የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ የመጀመሪያ የምስረታ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡
ኮሚቴው የተቋቋመው የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ሂደት፣ የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ ስትራቴጂ እና የሰቆጣ ቃልኪዳንን ለማስተባበር፣ ፖሊሲዎችን እና የሕግ ማዕቀፎችን ለመምራት መሆኑ ተገልጿል።
ይህ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አስራ አምስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ሲሆን በግብርና እና ጤና ሚኒስትሮች የሚመራ መሆኑም በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል፡፡
የምስረታ ጉባኤ ስብሰባ አስመልክቶም ስትሪንግ ኮሚቴውን በበላይነት የሚመሩት የጤና እና ግብርና ሚኒስትሮች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን መፍታት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመከላከል ኮሚቴው እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሠ በዚሁ ወቅት፤ በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት እና ስነ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ በ2012 ዓ.ም ወደ ትግበራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡
ይህም የኢትዮጵያን የምግብ ስርዓት ለመቀየር፣ ምርትና ምርታማነትን ለመሻሻል እንዲሁም ጤናማ ምግቦችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ስራዎች ከስርዓተ ምግብ ማሻሻል ጋር ተቀናጅተው እንዲተገበሩ እንደሚደረግም ነው የጠቆሙት፡፡
ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት፡፡
ስትሪንግ ኮሚቴው የምግብ ስርዓት እና ስነ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ወደ ትግበራ ከማስገባት ባሻገር የሰቆጣ ስምምነት ቃል ኪዳንም እንዲተገበር ይመራል ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው ኮሚቴው በፍኖተ ካርታው ውስጥ የተመላከቱ ውጤት ቀያሪ መፍትሄዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ይሰራል ብለዋል፡፡
ይህን የሚደግፉ የቴክኒካል ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ገልጸው፤ መሰል አደረጃጀት በክልል ደረጃ እንደሚቋቋምም ተናግረዋል፡፡
የምግብ ስርዓት እና ስነ ምግብ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታው በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀርቦ አድናቆት ማግኘቱንም ገልጸዋል፡፡
በፍኖተ ካርታው ችግሮች የተለዩ ሲሆን፤ ይህን መሰረት በማድረግም የመፍተሄ አቅጣጫዎች እና የትግበራ መርሃ ግብሮች ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት፡፡
የፍኖተ ካርታውን ዝግጅት በበላይነት የመሩት የስነ ምግብ ባለሙያው ዶክተር ጌታቸው ድሪባ፤ የዜጎችን የምግብ ፍላጎት ለማሟላት ምርትና ምርታማነት ከማሻሸል ባሻገር ጤናማ ምግቦች ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በሌላ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችና ሎጂስቲክስ ማዕከላት ሊስፋፉ ይገባል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት እና ስነ ምግብ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ቀረጻ ላይ ከ40 ተቋማት የተውጣጡ ከ120 በላይ ባለሙያዎች መሳተፋቸው ነው የተገለጸው።
የምግብ ዋጋ ንረትን ማረጋጋት እና ጤናማ አመጋገብን ማበረታታት እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቶችን መጠበቅ ሌሎች በአጀንዳው የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው።
በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የጤና፣ የግብርና፣ ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን፣ የትምህርት፣ የኢንዱስትሪ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ፣ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።